ሪፖርት | 48ኛው የሸገር ደርቢ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በመጀመሪያው አጋማሽ የተቆጠሩ ግቦች የምሽቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በ1-1 ውጤት እንዲቋጭ አድርገዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ አማኑኤል ተርፉን አሳርፎ አብርሃም ጌታቸውን ሲጠቀም ኢትዮጵያ መድንን ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በፍቃዱ ዓለማየሁ ፣ ዋሳዋ ጄኦፍሪ ፣ ሬድዋን ናስር እና መስፍን ታፈሰን በወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ ይታገሱ ታሪኩ እና አንተነህ ተፈራ ምትክ ወደ ቀዳሚ አሰላለፉ አምጥቷል።

የኢትዮጵያ ቡና ቡድን አባላት ለታላቁ ፊዚዮቴራፒት ይስሀቅ ሽፈራው ባደረጉት የወርቅ ሀብል እና የባለሙያውን ምስሎች ያካተተ ስጦታ አሀዱ ያለው ጨዋታ ሞቅ ያለ አጀማመር ታይቶበታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀኝ በተገኑ ተሾመ ኢትዮጵያ ቡናዎች በግራ በመስፍን ታፈሰ አመዝነው በማጥቃት እሳቤ በጀመሩት ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉት ቡናዎች አየል ብለው ታይተዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ መልሶ ማጥቃት ሳጥን ውስጥ ደርሰው መሐመድኑር ናስር ከአብዱልከሪም ወርቁ የደረሰውን ኳስ ሞክሮ ወደላይ የተነሳበት አጋጣሚ የቡድኑ ቀዳሚ አይነ ግቡ ሙከራ ነበር።

የቅዱስ ጊዮርጊስን እንቅስቃሴ በማቋረጥ በፈጣን ቅብብሎች ወደ ማጥቃት ዞን በመግባት እየጎላ የመጣው የቡና ጥቃት 16ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። ዋሳዋ ጄኦፍሪ ከመሀል የላከውን እና መሐመድኑር ያወረደውን ረጅም  ኳስ መስፍን ታፈሰ ከግራ ወደ ውስጥ አሳልፎለት ራሱ መሐመድ ኑር ናስር በጊዮርጊስ ተከላካዮች መሀል ተረጋግቶ ግብ አድርጎታል።

የፈረሰኞቹ የተከላካይ መስመር መዘናጋት 28ኛው ደቂቃ ላይም ለሌላ ግብ መንስኤ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። የብሩክ ታረቀኝን መዘናጋት ተከትሎ ሳጥን ውስጥ ከኋላው ተንስቶ ኳስ ያገኘው አማኑኤል አድማሱ ያደረገው ሙከራ ጎል ከመሆን የዳነው በፍሪምፖንግ ክዋሜ የመጨረሻ ጥረት ነበር። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አልፎ አልፎ ከተከላካይ መስመር ጀርባ የሚጣሉ እና ወደ ተገኑ የሚደርሱ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ሲቃረቡ ቢታይም ቡድኑ የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችል ቆይቷል። የኢትዮጵያ ቡና ጥቃትም ከመጀመሪያው ቀዝቀዝ እያለ ቢሄድም በማጥቃት ሽግግር ወቅት ከመሀል ወደ ግራ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ወደነበረው መስፍን ያደሉ አደገኛ ኳሶች የሚላኩባቸው ቅፅበቶች ይታዩ ነበር።

ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የአቻነት ግብ አግኝቷል። የኢትዮጵያ ቡናው በፍቃዱ ዓለማየሁ በቀጥታ ወደ ሆስፒታል እንዲያመራ ያስገደደውን ጉዳት ካስተናገደ በኋላ እምብዛም ሳይቆይ ነበር በአጭር ተጀምሮ በበረከት ወልዴ የተሻገረውን የማዕዘን ምት ሩቁ ቋሚ ላይ ነፃ ሆነው ከቆሙ የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች መካከል ፍሪምፖንግ ክዋሜ በግንባር በመግጨት አስቆጥሮ ቡድኑን ከዕረፍት በፊት ወደ አቻ ውጤት ማምጣት ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በሁለቱም አቅጣጫ ፈጣን ሽግግሮችን እያሳየን ሲጀምር በቀዳሚ አምስት ደቂቃዎች በቀኝ ከአማኑኤል አድማሱ የተነሱ ኳሶች ቡናን መሪ ለማረግ ተቃረበው ነበር። በተለይም 49ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ከአማኑኤል የመጣለትን ኳስ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር ሞክሮ ባህሩ ነጋሽ አድኖበታል። በቀጣይ ደቂቃዎች ፊት መስመር ላይ አማኑኤል ኤርቦን ቀይረው ያስገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከቀደመው የተሻለ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ በማድረግ የተጋጣሚያቸውን ጫና በተሻለ ሁኔታ መቀነስ ችለዋል።

78ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድኑር ናስር ወደ ግራ ካደላ የርቀት ቅጣት ምት እስካደረገው ሙከራ ድረስ ከጠንካራ ሙከራዎች ርቆ በቆየው ጨዋታ ቡድኖቹ ከመሀል ሜዳ ፍልሚያ ውጪ አንዳቸው የሌላኛቸውን የማጥቃት መስመሮች ተቆጣጥረው የቆዩባቸው እና አካላዊ ጉሽሚያዎች በርከት ያሉባቸው ነበሩ። ከፈጣን አጀማመራቸው አንፃር በአካላዊ ድካም ወደ ጨዋታው ፍፃሜ የደረሱት ቡድኖቹ ወደ ማብቂያው ላይ በሳጥኖቻቸው ውስጥ አደጋ የሚጋብዙ የመከላከል ስህተቶችን ሲሰሩ ታይቷል። በተለይም 90ኛው ደቂቃ ቡናዎች በሰነዘሩት ጥቃት መስፍን ታፈሰ ካመቻቸው ኳስ አንተነህ ተፈራ ጥሩ ዕድል አግኝቶ ኢላማውን ያልጠበቀበት ቅፅበት የጨዋታው ልዩነት ሊሆን ተቃርቦ ነበር። ያም ቢሆን ጨዋታው በ1-1 ውጤት ፍፃሜውን ማግኘቱ አልቀረም።

አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ጫና ፈጥረው ቢጀምሩም ለጨዋታው የሰጡት ከፍተኛ ግምት እንዳቀዛቀዛቸው ገልፀው በቡድናቸው አለመረጋጋት እና ጉጉት መታየታቸውን በውጤቱም ደስተኛ እንዳልሆኑ ጠቁመዋል። አሰልጣኝ ደረጄ ተሰፋዬ ደግሞ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እንዳደረጉ ያላቸውን እምነት በመጥቀስ የግብ ዕድሎችን በመፍጠራቸው ደስ መሰኘታቸውን አንስተው ከስብስባቸው ጥልቀት ማነስ አንፃር ተጫዋቾቻቸው ጥሩ መንቀሳቀሳቸውን አስረድተዋል።