የውጣ ውረድ ዘመን ፍፃሜን ፍለጋ…

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል ፤ በሰንጠረዡ አናት የሊጉን ክብር ለመቆናጠጥ የሚደረገው ትንቅንቅ እጅግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። አዲሱ የሊጉ አሸናፊ ማን ይሆን ?

በወቅታዊ የሊጉ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ58 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተፎካካሪያቸው መቻል በአንድ ነጥብ አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ፤ በመጪዎቹ ሁለት መርሐግብሮች መቻል አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ሻሸመኔ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድንን ይገጥማሉ።

እኛም በሁለቱ የዋንጫ ተፎካካሪ ክለቦች ዙሪያ እና በዋንጫ ፉክክሩ ዙሪያ የተወሰኑ ሀሳቦችን ልናነሳ ወደድን።

👉 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረበት ከ1990 አንስቶ በሊጉ ቤተኛ ከነበሩ ስሞች መካከል አንዱ የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ባንኮች ስፖርት ማኅበር በአሁኑ አጠራሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2009 የውድድር ዘመን ሳይጠበቅ ከሊጉ መውረዱን ተከትሎ የወንዶች ቡድኑ ህልውና እስከ መፍረስ መድረሱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

በ2014 ዳግም የተቋቋመው ቡድኑ ከሁለት የውድድር ዘመናት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ በተመለሰበት የዘንድሮው የውድድር ዘመን በዚህ ልክ ተፎካካሪ ይሆናል ብሎ የገመተ አልነበረም። ለወትሮውም ቢሆን በፋይናንስ አቅሙ የማይታማው ክለቡ በክረምቱ በርከት ያሉ ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች ማዘዋወር የቻለ ሲሆን በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና አሰልጣኝነት የመምራት ዕድል ባገኘው አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ እየተመራ የጀመረው ዓመት ነበር።

ዘጠኝ ተከታታይ ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች አድርገው በመልካም አጀማመር ሊጉን የጀመሩት ባንኮች የመጀመሪያው ዙር አካሄዳቸው ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚዘልቁ አመላካች ነበር። ለረዥም ጊዜያት የሊጉን መሪነት ተቆናጠው የከረሙት ንግድ ባንኮች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የከሰሯቸው አራት ነጥቦች አጣብቂኝ ውስጥ ቢከታቸውም ለዋንጫ የሚያደርጉትን ጉዞ የመወሰኑ ስልጣን ግን አሁንም በእጃቸው ነው። ቡድኑ ቀንደኛ የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ተከታታይ ነጥብ በጣሉባቸው ወሳኝ በሚባሉ የጨዋታ ሳምንታት ወጥነት ባለው ብቃት ነጥቦች መሰብሰቡ እስከ 26ኛ ሳምንት ድረስ በተደላደለ ሁኔታ መሪነቱን ቢያቆናጥጠውም ተከታታይ የጣላቸው ነጥቦች የዋንጫ ፉክክሩ መልክ የቀየሩ ነበሩ።

ሀምራዊ ለባሾቹ በውድድር ዓመቱ የነበራቸው ወጥነት የቡድኑ ዋነኛ መለያ ነው፤ በተለይም በሊጉ ጅማሮ እንዲሁም እስከ 26 ሳምንት ዘልቆ የነበረው ተከታታይ ድሎች በዋንጫ ጉዞው ላይ ልዩነት ፈጣሪ ወቅት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ሰፊ እና አማራጨ ብዙ ግብ ማስቆጠር ኃላፊነት እና የመከላከል ጥንካሬ ቡድኑ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለዋንጫ እንዲፎካከር ያስቻሉ ጥንካሬዎች ናቸው። ቡድኑ ከግለ-ሰባዊ ብቃት ይልቅ እንደ ቡድን መዋቀሩ ባይካድም በእያንዳንዷን ደቂቃ ሜዳ ላይ ቆይቶ ቡድኑን ያገለገለው ፈቱዲን ጀማል ፣ ባሲሩ ዑመርና የመጨረሻ ሳምንታት የቡድኑ የነብስ አዳኝ የነበረው አዲስ ግደይ አስተዋጽዖ ግን የጎላ ነበር።

የቡድኑ አመጣጥ እንዲሁም ጥቂት ብትሆንም በሁለቱም ቡድኖች መካከል ያለችው የአንድ ነጥብ ልዩነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ባንክ ዕድሉን የመውሰን ዕጣ በእጁ እንዳለ አመላካች ቢሆንም
በቀሩት ሁለት መርሐግብሮች በጎ ለውጡን በውጤት መመንዘር ካልቻለው፤ ላለመውረድ የሞት ሽረት ትግል ያደርጋል ተብሎ ከሚጠበቀው ሻሸመኔ ከተማ እና ግቦችን እያዘነበ ድሎቹን በማጣጣም ላይ ከሚገኘው ኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር መሆኑ ፈተናውን ከባድ ያደርገዋል።  ከሻሸመኔ ከተማ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በወረቀት ደረጃ ቀላል ሊመስል ቢችልም የቅርብ ሳምንታት የቡድኑን ዕድገት በቅርበት ላስተዋለ ግን ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆን መገንዘብ ይችላል። አሥራ ሰባት ግቦች በማስቆጠር ተከታታይ ጨዋታዎች ያሸነፈው ኢትዮጵያ መድንም ሌላው በንግድ ባንክ የዋንጫ መንገድ የቆመው ጠንካራ ቡድን ነው።

👉 መቻል

የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት እያከበረ የሚገኘው መቻል በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስፖርት ታሪክ ውስጥ የጎላ አበርክቶ ከነበራቸው የስፖርቱ ዘርፍ ባለውለታዎች አንዱ ነው። በእግርኳሱ ግን በቀደመው ጊዜ ገናና ስም የነበረው ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ያ የቀደመ ሞገሱ አብሮት አለ ለማለት አያስደፍርም።

ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርደው የተመለሱት መቻሎች ባለፉት ዓመታት የተሻለ ቡድን ለመገንበት በማለም የተለያዩ መንገዶችን ሲሞክሩ ቢቆዩም በክረምቱ ያደጉት መዋቅራዊ ለውጥ በብዙ መልኩ ቡድኑን ወደፊት ያሻገረ ይመስላል። በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የቴክኒክ ዳይሬክተርነት የተለያዩ ሙያተኞችን ጨምሮ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን ወደ አሰልጣኝነት በማምጣት የተሻለ ስብስብን ለመገንባት ጥረት አድርገዋል፤ በተለይም ቁልፍ ቦታዎች ላይ የተደረጉ ለውጦች ለወትሮ ጥሩ ስብስብ ቢይዝም ውጤት ማምጣት ላልቻለው ቡድን ውጤታማ አድርገውታል።

ጦሩ በመጀመርያው ዙር ድንቅ እንቅስቃሴ ካደረጉ ክለቦች አንዱ ነው። ቡድኑ ከመክፈቻው ድል በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ቢጥልም ከዛ በኋላ በተከናወኑ መርሐግብሮች ግን አምስት ጨዋታዎች በመደዳ ከማሸነፍ ባለፈ በአስራ አንድ ጨዋታዎች ሽንፈት ሳይቀምስ ዘልቋል። በመጀመሪያው ዙር የነበረው ጥንካሬም ማግኘት ከሚገባው 45 ነጥብ 12 ብቻ በመጣል በ33 ነጥቦች ዙሩን በመሪነት እንዲያጠናቅቅ አስችሎት ነበር። ሆኖም ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደው በጀመሩት ሁለተኛው ዙር በርከት ያሉ ነጥቦች መጣላቸውን ተከትሎ መሪነታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል።

መቻል በ26ኛው ሳምንት ውድ ሁለት ነጥቦች መጣሉ በፉክክሩ አንድ እርምጃ ወደ ኋላ እንዲቀር ከማስቻሉም ባለፈ የዋንጫ ፉክክሩ ያበቃለት መስሎ ነበር። ሆኖም ንግድ ባንክ በተከታታይ የጣላቸውን ነጥቦች የጦሩን የዋንጫ ተስፋ አለምልሞታል። መቻል ሁለት ጨዋታዎች ብቻ በሚቀሩት ሊግ ከመሪው በአንድ ነጥብ ርቆ መገኘቱን ተከትሎ ለዋንጫ ያለውን ተስፋ ንግድ ባንክ በሚገጥመው የነጥብ መንሸራተት ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም ልዩነቱ ወደ አንድ መጥበቡን ተከትሎ የዋንጫ ዕድሉ ከባለፉት ሳምንታት ጨምሯል።

ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ከውጤታማነት በዘለለ ብዙም አዝናኝ የሚባል ቡድን አልነበረም። ከፍ ያለው የውጤታማነት ደረጃው እና በዛ ሂደት ውስጥ የነበረው ወጥ አቋምም በዚህ ደረጃ እንዲፎካከር አስችሎታል ተብሎ ይታመናል። በሁለተኛው ዙር የአጨዋወት መንገድ ለውጥ አድርገዋል። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሰባት መርሐግብሮች ያላቸውን ሰፋ ያለ እና ጥራት ያለው የተጫዋቾች ክምችት ያማከለ፤ አማካዮቹን በቀጥር አብዝቶ ማጥቃቱ ላይ የሚያሳትፍ አጨዋወት መተግበራቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል። የአጨዋወት ለውጡ ቡድኑ በጎሎች የታጀበ፣ አዝናኝ እና በፋታ የለሽ የማጥቃት አጨዋወት የተቃኘ ከማድረጉም ባለፈ ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑ ያሳየበት ነው። መቻል በቁጥር በርከት ያሉ ተጫዋቾች የሕይወት ዘመናቸው ምርጡ የውድድር ዓመት ያሳለፉበት ቡድን ነው፤ በተለይም አማካዩ ከነዓን ማርክነህ፤ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ምንይሉ ወንድሙ፤ እያንዷንዷን ደቂቃ ቡድኑን ያገለገለው ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፍያን እንዲሁም ሽመልስ በቀለ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ሆነው ቡድኑን እስከመጨረሻው ለዋንጫ እንዲፎካከር አስችለውታል። በቀጣይ አስፈሪ የማጥቃት ክፍል ያለው አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማን ያስተናግዳል።

1990 ላይ መብራት ኃይል እና ኢትዮጵያ መድን ፣ 1995 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ ፣ 1996 ላይ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ፣ 2003 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ፣ 2010 ላይ ጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ 2011 ላይ መቐለ 70 እንደርታ ፣ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና ፣ 2014 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ የውድድር ዓመቱ ጉዟቸውን በመጨረሻ ቀን የዋንጫ ፍጥጫ አገባደዋል። ዘንድሮም የዛሬዎቹን ጨዋታዎች ተከትሎ በ 30ኛው ሳምንት ተመሳሳይ ትዕንት ልናይ የምንችልበት ዕድል ይኖራል። አልያም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የራሱን ጨዋታ አሸንፎ እና የመቻልን ሽንፈት ጠብቆ ዛሬ ቻምፒዮን ሊሆን የሚችልበት ዕድልም ይኖራል። እነዚህ እርግጥ ያልሆኑ እውነታዎች ቢሆኑም ዘንድሮ አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በአዲስ ፎርማት ከጀመረ 26ኛ የውድድር ዓመቱ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን የመዘገባቸው ስምንት ቻምፒዮን ክለቦች ዝርዝር ውስጥ ዘንድሮ አንድ አዲስ ስም ጨምሮ መፃፉ የማይቀረው እውነታ ነው።

በሊጉ ታሪክ በተለያዩ ጊዜያት ከፍ ሲል ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው በተቃራኒው ደግሞ የውጣ ውረድ ወቅቶችን አሳልፈው ለዛሬ ከደረሱት ሁለቱ ክለቦች መካከል ማን የሊጉን ክብር ያነሳል ? በቀሪ ጨዋታዎች ይመለሳል !