ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ በሊጉ መሰንበቱን አረጋግጧል

ወልቂጤ ከተማ በሁለቱም አጋማሾች ባስቆጠሯቸው ግቦች ሀምበሪቾን 2ለ0 በመርታት በፕሪምየር ሊጉ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል።

በሊጉ የ28ኛ ሳምንት መርሀግብር ሀምበሪቾ ዱራሜ ከወላይታ ድቻ ጋር ያለ ጎል ካጠናቀቀው ስብስቡ አንድም ተጫዋች ሳይቀይር ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ ከሀዋሳ ከተማ ጋር 2ለ2 ተለያይተው በነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በኩል ግን የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ የተደረገ ሲሆን ዋሀቡ አዳምስ ፣ ሙሉአለም መስፍን እና ተስፋዬ መላኩ ወጥተው በምትኩ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ጋዲሳ መብራቴ ተተክተዋል።

በፕሪምየር ሊጉ ለከርሞ ለመሰንበት ወሳኝነቱ ከፍ ባለው እና በተመሳሳይ ሰዓት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና ከጅምሩ ወልቂጤ ከተማዎች ኳስን በመቆጣጠር በይበልጥ ከመስመር መነሻቸው በማድረግ ጫናዎችን ከፍ ባለ የራስ መተማመን ሲያሳድሩ ተንፀባርቋል። 16ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ዳንኤል ደምሱ አሻምቶ ሳምሶን ጥላሁን ባደረጋት እና ምንታምር መለሠ ባዳናት ሙከራ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ሠራተኞቹ 19ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ ግብ አግኝተዋል።

በጥሩ የእግር ስራ በቀኝ መነሻዋን ያደረገችን ኳስ ጋዲሳ እና ተመስገን ተቀባብለው ለማለፍ ሲሞክሩ ኳሷን በተሳሳተ አቅጣጫ የሀምበሪቾ ተከላካዮች ጨርፈው እግሩ ስር ያገኛትን ኳስ መድን ተክሉ መረቡ ላይ አሳርፎ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ለጨዋታ ምቹ ባልነበረው አየር በቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ ሀምበሪቾዎች በጥብቅ መከላከል ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ቢጥሩም በቀላሉ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መግባቱ ላይ ተስኗቸው ተመልክተናል። በቀሩት ደቂቃዎች ኳስን ወደ ራሳቸው በማድረግ ብልጫ መውሰድ ላይ የበረቱት ወልቂጤዎች ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ የርቀት እና የቅጣት ኳሶች ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ቢሞክሩም ጨዋታው በ1ለ0 የወልቂጤ መሪነት ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሲቀጥል ተመጣጣኝ መልክ የነበረውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለጥቂት ደቂቃዎች ካስመለከተን በኋላ በሂደት የተጫዋችን ለውጥን በማድረግ መሐል ሜዳው ላይ ጥሩ ይዘትን መፍጠር ወልቂጤ ከተማዎች ከጀመሩ በኋላ በሁለቱ ኮራደሮች በጥልቀት በሚደረጉ አጨዋወቶች በተሻለ ንቃት ብልጫን ወስደው ተስተውሏል። ለኋላ መስመራቸው ሽፋን ከመስጠት በስተቀር ወደ ፊት ሳብ ብሎ ጥቃት ለመሰንዘር አይናፋር የነበሩት ሀምበሪቾዎች በሰሩት የአደራደር ክፍተት ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል። 67ኛው ደቂቃ ከመሐል መነሻዋን ያደረገችን ኳስ ከቀኝ አዳነ በላይነህ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ የሰጠውን ኳስ ጋዲሳ መብራቴ ተረጋግቶ ሁለተኛ ጎልን ከመረቡ ጋር ደባልቆታል።

2ለ0 ከሆነ በኋላ መቀዛቀዞችን እየታየበት በቀጠለው ጨዋታ በቀሩት ደቂቃዎችም ሜዳ ላይ ከሚታዩ እንቅስቃሴዎች ውጪ በሙከራዎች መታጀብ ሳይችል በወልቂጤ አሸናፊነት ተቋጭቷል። ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ መሰንበቱን ሲያረጋግጥ በአንፃሩ ሻሸመኔ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ወርዷል።