ሪፖርት | ሀምራዊ ለባሻቹ ወደ ዋንጫው አንድ እርምጃ የሚያስጠጋቸው ወሳኝ ድል ተጎናፀፉ

ሁለት አዲስ አዳጊ ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማን ወደ ከፍተኛው ሊጉ ሲሸኝ ንግድ ባንክ ወደ ዋንጫው አስጠግቷል።

ንግድ ባንኮች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ከተለያየው አሰላለፍ ሲሞን ፒተር በቢንያም ጌታቸው ተክተው ሲገቡ ሻሸመኔ ከተማዎችም በፋሲል ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድን ኬን ሳይዲ፣ የአብስራ ሙሉጌታ፣ ወጋየሁ ቡርቃ እና ማይክል ኔልሰን በአቤል ማሞ፣ ያሬድ ዳዊት፣ ምንተስኖት ከበደና ጌታለም ማሙዬ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክርና ጥቂት የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት የመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ንግድ ባንኮች ከጨዋታው ጅማሮ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው ቢጫወቱም የተጋጣሚን ጠጣር የመከላከል አልፈው በርካታ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። በሂደት ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ሻሸመኔ ከተማዎችም ብልጫ በወሰዱባቸው ደቂቃዎች ያለቀለት ዕድል አምክነዋል። እዮብ ገብረማርያም በግሉ ጥረት ከመስመር አሻግሯት ሁዛፍ ዓሊ ያልተጠቀመባት ወርቃማ ዕድልም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። በአርባኛው ደቂቃ ግን ንግድ ባንኮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል፤ ቡድኑ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግሮ ከቆዩ በኋላ ባሲሩ ዑመር አሻምቷት ሱሌይማን ሐሚድ ባስቆጠራት የግንባር ጎል መሪ መሆን ችለዋል።

በብዙ መመዘኛዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሻሸመኔ ከተማዎች ይበልጥ ተዳክመውና የተጋጣሚን ጥቃት ለመመከት ተቸግረው ሲታዩ ንግድ ባንኮች በአንፃሩ ፍፁም ብልጫ ወስደው እጅግ በርካታ የግብ ሙከራዎችም አድርገዋል። ፉዐድ ፈረጃ ከርቀት አክርሮ መቷት አቤል ማሞ እንደምንም ባወጣት ለግብ የቀረበች ሙከራና ተጫዋቹ ከቆመ ኳስ በፈጠራት ዕድል ግብ ለማግኘት ጥረት ያደርጉት ንግድ ባንኮች በስልሣ ሶስተኛው ደቂቃ ላይ በአዲስ ግደይ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል።

በተለመደው ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በርካታ ዕድሎች የፈጠረው ቡድኑ ከተጠቀሰው ጥንካሬ በተጨማሪ ከኳስ ውጭ የነበረው የተደራጀ አጨዋወት በአወንታ የሚጠቀስለት ጎኑ ነበር። ይህንን ተከትሎም ሻሸመኔ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል እንዳይፈጥር አድርጎታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ዕድሎች መፍጠራቸውን የቀጠሉት ባንኮች በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል በተለይም በአዲስና ዳዊት የተግባቦት ችግር የመከነች ዕድል የግን መጠኑን ወደ ሦስት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ተጠባቂው ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሻሸመኔ ከተማ ባደገበት ዓመት ወደ ታችኛናው ሊግ መውረዱ ሲያረጋግጥ ንግድ ባንክ የዋንጫውን አንድ እጀታ የጨበጠበት ድል አስመዝቧል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሀሳባቸው የሰጡት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ እንዳሳዩ አምነው ሽንፈቱ ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል። ቀጥለው ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ጨዋታው የሞት ሽረት እንደነበር በመግለፅ ውጤቱ ይበልጥ ወደ ዋንጫው የሚስጠጋቸው እንደሆነና ለዋንጫ የሚደረገው ፉክክር አሁንም ገና እንደሆነ ጠቅሰዋል።