“ተረስተናል……”

“የብዙ ወራት ደመወዝ ስላልተከፈለን በችግሮች እየተፈተንን ነው ፤ ትኩረት ተነፍጎናል።” ሲሉ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ በርካታ ተጫዋቾች ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

የ2016 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያውን ዙር በሀዋሳ ከተማ አጠናቆ ለሁለተኛው ዙር ውድድር ወደ አዳማ በማቅናት አሁን ሙሉ ውድድሩን ለማገባደድ የሦስት ጨዋታዎች ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል።

ቻምፒዮን ለመሆን እና ወደ ከፍተኛ ሊጉ ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ ፉክክሩ እያየለ ቢቀጥልም በብዙ ፈተናዎች ታጅበው በትዕግስት ያላቸውን አቅም ሁሉ የሰጡት ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሴት ተጫዋቾች አሁን ለከፋ ችግር ተጋልጠናል እያሉ ነው።


ከተወሰኑ የተደራጁ ክለቦች ውጪ የደመወዝ ክፍያ ችግር በብዙ ክለቦች ላይ እየተስተዋለ ቢሆንም የስድስት ወር ደመወዝ ያላገኙት የሀምበርቾ ተጫዋቾች እና የሰባት ወር ደመወዝ ያላገኙት የይርጋ ጨፌ ቡና ተጫዋቾች ይበልጥ የተቸገሩት ናቸው።

ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታችንን አስገብተን ውሳኔ ብንጠይቅም መፍትሔ ልናገኝ አልቻልንም ያሉት ተጫዋቾቹ ቤተሰብ ልናግዝ ወጥተን ድጋሚ እነሱን ገንዘብ በመጠየቅ እያስቸገርን ቀጥለናል ይላሉ። እነዚህ ተጫዋቾች አክለውም ከሜዳ ወደ ማረፊያቸው ሲመለሱ መታጠቢያ ሳሙና እስኪያጡ እና እንደ ንጽሕና መጠበቂያዎች ላሉ በሴትነታቸው ለሚያስፈልጓቸው ተጨማሪ ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ ማጣታቸውን ሲገልጹ በሚያርፉበት ሆቴል አልፎ አልፎ የምግብ ማቋረጥ ሲስተዋል እንደነበር ተናግረዋል።

ፕሪሚየር ሊጉ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሲጠናቀቅ ወደ ቤታቸው የሚበተኑት ተጫዋቾች ይህንን ችግር መች እንደሚፈታላቸው ማረጋገጫ ሳያገኙ ወደ ቤት መሄድ እና አንድም የቡድን አመራር መጥቶ ችግራቸውን ጠይቆ አለመረዳቱ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገባቸው በመጠቆም የስፖርቱ ቤተሰብ ትኩረት ባጣው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚታዩ የመብት ጥሰቶችን ለይቶ ድምፅ እንዲሆናቸው አበክረው ተማጽነዋል።


በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል ባገኘነው መረጃ መሠረት ፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የሚወስነውን ውሳኔ ለማስፈጸም ቁርጠኛ ከመሆኑ ባሻገር በርካታ ውስብስብ ጉዳዮችን ለመፍታት ደሞዝ የመክፈል ችግር ያለባቸው ክለቦችን በአካል ወደየክለቦቹ መቀመጫ ከተሞች በማምራት እና በመነጋገር መፍትሔ ለማምጣት እየተጋ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

* የይርጋ ጨፌ ቡና እና ሀምበርቾ የክለብ አመራሮችን በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካልንም። ሆኖም የእነሱን ሀሳብ ለመቀበል በራችን ክፍት መሆኑን እናሳውቃለን።