የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።
አሰላለፍ 4-4-2 ( Diamond )
ግብ ጠባቂ
ምንተሰኖት ጊምቦ – ሀዋሳ ከተማ
ሀዋሳ ከተማ በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት ከባህር ዳር ጋር 1ለ1 ባጠናቀቀበት ጨዋታ ከአንድ ዓመት በላይ ጉዳት የተመለሰው የግብ ዘቡ በያዝነው የጨዋታ ሳምንት በቋሚነት በተሰለፈበት የመጀመሪያ የዓመቱ ጨዋታው ጥሩ ጊዜ አሳልፏል። ባህር ዳሮች በተደጋጋሚ በሽግግር የጨዋታ መንገድ ከዕረፍት በፊት እና ከዕረፍት መልስ የፈጠሯቸውን ግልፅ የግብ ዕድሎችን በድግግሞሽ ያመከነው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ደብዞዞ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ልዩነት ፈጥሮ በመገኘቱ በሳምንቱ የምርጥ ስብስባችን አካል ሆኗል።
ተከላካዮች
ሱሌይማን ሐሚድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ንግድ ባንክ ሻሸመኔ ከተማን አሸንፎ ወሳኝ ነጥብ ባገኘበት መርሐግብር ላይ ወሳኝ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ሱሌይማን ሐሚድ የቡድኑን ዐይን ገላጭ የሆነች የግንባር ግብ በማስቆጠር የጨዋታውን ሁለንተናዊ ገፅታ የቀየረ ወሳኝ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ተጫዋቹ በጨዋታው ካሳየው እንቅስቃሴ ባሻገር በዕለቱ ያስቆጠራት ግብ ወሳኝነት በሳምንቱ ምርጥ ቡድን እንዲካተት አስችሎታል።
ፍሪምፖንግ ክዋሜ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሽግሽግ የፈረሰኞቹ የመሃል ተከላካይ ሆኖ ሸገር ደርቢን ያደረገው ጋናዊው አማካይ በጉዳት ጨዋታውን መጨረስ ባይችልም በቆይታው ጥሩ አስተዋፅኦ አድርጓል። ወሳኟን የአቻነት ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ያለቀለት ኳስ ከግብ በማውጣት እና በተዳከመው የኋላ መስመር በግሉ አደጋን ለመቀነስ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነበር።
ወንድሜነህ ደረጄ – ኢትዮጵያ ቡና
በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው የሸገር ደርቢ የመሃል ተከላካዩ የነበረው ንቃት እና መረጋጋት ቡድኑን ከከባድ ጥቃቶች መታደግ የቻለ ነበር። ትክክለኛ ጊዜ እና ቦታ ላይ በመገኘት የሚወስዳቸው እርምጃዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነት የበላይነትን እንዲወስድ እና ከባድ ጥቃቶችንም በማቋረጥ ቁልፍ ሚና እንዲወጣ አድርገውታል።
ደስታ ዮሐንስ – ሲዳማ ቡና
ደስታ ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 2-0 ያሸነፈበት ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ለአንድ ጎል መንስኤ መሆኑ እና ሌላኛውን ማስቆጠሩ ዋና ተዋናይ ሲያደርገው በቀሪ ደቂቃዎችም በቡድኑ የግራ መስመር በነፃነት ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ እና የማጥቃት ተሳትፎው ልዩ ሆኖ ታይቷል።
አማካዮች
ባሲሩ ዑመር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ከንግድ ባንክ ጋር መልካም የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ባሲሩ ዑመር በጨዋታ ሳምንቱ ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረጉ አማካዮች አንዱ ነው። ተጫዋቹ ቡድኑ ንግድ ባንክ ሻሸመኔ ከተማን አሸንፎ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ቁልፍ ሚና በተጫወተበት መርሐግብር አንድ ጎል የሆነ ኳስ አመቻችቶ ሲያቀብል የቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ በመሆንም ለበርካታ የግብ ዕድሎች መነሻ ነበር። ሀምራዊ ለባሾቹ ውድ ሦስት ነጥብ በሸመቱበት ጨዋታ ያበረከተው አስተዋፅኦም በሳምንቱ ምርጥ ቡድን አካትቶታል።
ወገኔ ገዛኸኝ – ኢትዮጵያ መድን
ደካማ እንቅስቃሴ በሙሉ ዘጠና ደቂቃ በተስተዋለበት የመድን እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ በጨዋታው ነብስ ከዘሩ ተጫዋቾች መካከል አማካዩ ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። ብዙም ሳቢ ያልሆነ እና አጥጋቢ የግብ ዕድሎች ባልነበሩበት ጨዋታ በግሉ ጥሩ ቀን ከማሳለፉ በተጨማሪ መድኖች ሦስት ነጥብን ይዘው እንዲወጡ ያስቻለውን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር መቻሉን ተከትሎ በቦታው ምርጥ ተሰኝቷል።
ሽመልስ በቀለ – መቻል
መቻል በአዳማ ከተማ ላይ እጅግ ወሳኝ ድልን ሲቀዳጅ ሽመልስ የዓመታት ማንነቱን ያንጸባረቀ የጨዋታ ቀን አሳልፏል። ለቀዳሚ ሁለት ጎሎች ከነበረው አስተዋፅኦ እና በአማካይ ክፍል ቡድኑ ብልጫ እንዲወስድ ካደረገው ጥረት በተጨማሪ ምሽቱን የግል ብቃቱን የምታሳይ እጅግ ድንቅ ጎል (solo goal) በማስቆጠር አሳርጓል።
መድን ተክሉ – ወልቂጤ ከተማ
ወልቂጤ ከተማ በሊጉ መቆየቱን ባረጋገጠበት የሀምበርቾው መርሐግብር ምንም እንኳን ጨዋታው ወረድ ያለ ፉክክርን ቢያስመለክተንም እንደ ቡድንም ሆነ በግል ደረጃ ጥሩ ቀን ካሳለፉ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ ወጣት አማካይ ነበር ማለት ይቻላል። ጥሩ እንቅስቃሴን ከማድረግ ባሻገር ቡድኑ 19ኛው ደቂቃ ላይ መሪ እንዲሆን ያስቻለውን ግብም ማስቆጠር ችሏል።
አጥቂዎች
በረከት ደስታ – መቻል
በዘንድሮ የመቻል እንቅስቃሴ ውስጥ በተለይ በመጀመሪያው ዙር በተለያዩ ምክንያቶች ደካማ ጊዜን ያሳለፈው በረከት ደስታ በሁለተኛው ዙር በተለይ በመጨረሻዎቹ ጥቂት ሳምንታት ግን የቀደመው በረከት ደስታን እያስመለከተን ያለ ይመስላል ፤ አስደናቂ ግብን በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ማስቆጠር የቻለው በረከት በግራ መስመር ባዘነበለው የመቻል ማጥቃት ውስጥ ቁልፉ ሰው ነበር።
መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና
በሸገር ደርቢ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በግራ የኢትዮጵያ ቡና ዋነኛ የማጥቃት መሳሪያ የነበረው መስፍን ለጊዮርጊስ የቀኝ መስመር ፈተና ሆኖ ነበር። በጨዋታው ብቸኛውን ግብ ያመቻቸው መስፍን ከኳስ ጋር በሚገናኝበት ወቅት ፍጥነት እና የግል ክህሎቱን በመጠቀም ተደጋጋሚ አደጋዎችን ፈጥሯል።
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል
መቻሎች አዳማ ከተማን 3ለ0 አሸንፈው መሪው ንግድ ባንክን እግር በእግር መከታተል ቀጥለው ቻምፒዮኑ ቡድን በመጨረሻው ቀን እንዲለይ ሲያስገድዱ በጨዋታው ዕለት ያደረጉት እንቅስቃሴ ድንቅ ነበር። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ከጨዋታው መጀመር አንስቶ በማያቋርጥ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው በመጫወት ቀድመው ጨዋታውን የተቆጣጠሩበት መንገድ ከአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ጋር ተፎካክረው ይህንን ምርጥ ቡድን እንዲመሩ አስችሏቸዋል።
ተጠባባቂዎች
ባህሩ ነጋሽ
ዋሳዋ ጂኦፍሪ
ኢማኑኤል ላሪዬ
ዮሐንስ መንግሥቱ
ዳዊት ተፈራ
መሐመድ ኑርናስር
አዱስ ግደይ
ጋዲሳ መብራቴ