ዓሊ ሱሌይማን የፕሪሚየር ሊግ ቆይታውን ባጠናቀቀበት የመጨረሻ ጨዋታ ኃይቆቹ በአጥቂው ሁለት ግቦች ታግዘው ወላይታ ድቻን በመርታት ዓመቱን በድል ፈፅመዋል።
በሊጉ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታ ሀዋሳዎች ከባህር ዳር ጋር 1ለ1 ከተለያዩበት አሰላለፍ ውስጥ የስድስት ተጫዋቾችን ለውጥን ሲያደርጉ ሠለሞን ወዴሳ ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ታፈሰ ሠለሞን ፣ አዲሱ አቱላ ፣ እዮብ አለማየሁ እና ቸርነት አውሽ አርፈው ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ሲሳይ ጋቾ ፣ ያሬድ ብሩክ ፣ አማኑኤል ጎበና ፣ እስራኤል እሸቱ እና ተባረክ ሄፋሞ በቋሚነት ተተክተው ገብተዋል። በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻዎች ከፋሲል ጋር ያለ ጎል ሲፈፅሙ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ውስጥ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ቢኒያም ገነቱን በአብነት ይስሀቅ ፣ ኬኔዲ ከበደን በአናጋው ባደግ እና ብዙአየው ሰይፉን በአበባየው ሀጂሶ የተደረጉ ለውጦች ናቸው።
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተማሪዎች ምርቃት የተነሳ መያዙን ተከትሎ የሜዳ ለውጥ ተደርጎ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ በተከናወነው የሊጉ የመጨረሻ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐግብር ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ በስዊድኑ ኦልሴፌንስካን እየተባለ በሚጠራው የሀገሪቱ ትልቁ ሊግ ተሳታፊ ለሆነው እና ዓመቱን አምስተኛ ሆኖ ለፈፀመው ጎቴቦርግስ አትሊቲ (GAIS) ክለብ የሦስት ዓመት ውል ለመፈረም በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ስፍራው ለሚያመራው የሀዋሳ ከተማ ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱለይማን ክለቡ የሽኝት መርሐግብርን ካደረገለት በኋላ ጨዋታው እንደጀመረ ገና 3ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበታል።
ተባረክ ሄፋሞ ከቀኝ ወደ ውስጥ የሰጠውን አማኑኤል ጎበና ተቀብሎ ከጀርባው ለነበረው ዓሊ ሱለይማን ሲሰጠው አጥቂው ከመረብ አዋህዶ ሀዋሳን መሪ አድርጓል። በእንቅስቃሴ ተመጣጣኝ አቀራረብ በታየበት ነገር ግን ሀዋሳ ከተማዎች ዕድሎችን በመፍጠሩ በተሻሉበት ቀጣይ ደቂቃዎች 21ኛው ደቂቃ ተባረክ ከቀኝ የሰጠውን ዓሊ በቀጥታ መቶ የግብ ዘቡ አብነት መክቶበታል።
30ኛው ደቂቃ ላይም ከሳጥኑ ጠርዝ የተገኘን የቅጣት ምት ዓሊ መቶ አብነት ካዳነበት ኳስ በኋላ በተወሰነ መልኩ ለማጥቃት አይናፋር ሆነው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት 35ኛው ደቂቃ በእዮብ ተስፋዬ አማካኝነት ጥሩ ዕድልን አግኝተው ምንተስኖት ጊምቦ በቀላሉ ይዞበታል። ጨዋታው ሊገባደድ ሲቃረብ በግብ ሙከራዎች በእጅጉ ተሽለው የታዩት ሀዋሳ ከተማዎች በያሬድ ብሩክ እና እስራኤል እሸቱ አማካኝነት ጥራት ያላቸውን ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን ቢፈጥሩም ግብ ጠባቂው አብነት ይስሀቅ አምክኗቸው አጋማሹም በሀዋሳ 1ለ0 መሪነት ተጋምሷል።
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በአማካይ ክፍል ላይ የተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገው መመለስ የቻሉ ሲሆን 47ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ብሩክ በአግባቡ የሰጠውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ከመረብ አሳርፎ የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ ሁለት አሳድጓል። ቀዝቀዝ ያሉ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ ከሙከራዎች ይልቅ ሜዳ ላይ የኳስ ቅብብሎች በዝተው የታየበት ሲሆን ወላይታ ድቻዎች የናታን ጋሻውን የቀኝ የሜዳ ክፍል ለመጠቀም ቢጥሩም ከአፈፃፀም አኳያ ደካሞች ሆነው ታይተዋል።
በአንፃሩ ዕድሎችን በተሻለ የሚፈጥሩት ሀዋሳዎች 70ኛው ደቂቃ ያሬድ ብሩክ ከግራ አክርሮ መቶ አብነት ያወጣበት እና ዓሊም መልካም አጋጣሚን ፈጥሮ ሳይጠቀምበት የቀረችው ሙከራ ትጠቀሳለች። እዮብ ተስፋዬ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከሀዋሳ ተከላካዮች እግር ስር ነጥቆ ወላይታ ድቻን ወደ ጨዋታ መለሰ ተብሎ ሲጠበቅ ካመከናት አጋጣሚ መልስ ጨዋታው በሀዋሳ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።