በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና በየኋላሸት ሠለሞን ግቦች 2ለ1 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት ዓመቱን በድል አጠናቀዋል።
በሊጉ የ29ኛ ሳምንት የጨዋታ ሳምንት ወቅት ሀድያ ሆሳዕና በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ያሬድ በቀለ ፣ ቃልዓብ ውብሸት እና ካሌብ በየነን ብቻ በማስቀረት በስምንቱ ላይ ቅያሪን ሲያደርጉ በሸገር ደርቢ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 1ለ1 ተለያይተው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አስራ አንዱንም ተጫዋቾች ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።
በኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ መሪነት በጀመረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ማጥቃት ላይ በጊዜ የበረቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች 2ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። አብዱልሐፊዝ ቶፊቅ ከቀኝ የደረሰውን ኳስ በጥሩ ዕይታ በተከላካዮች መሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ሳጥን ውስጥ በተረጋጋ መልኩ የተገኘው አንተነህ ተፈራ ጎል በማድረግ ቡናማዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
በቀጣዮቹ የጨዋታ ደቂቃዎች እንደ አጀማመራቸው መቀጠል ያልቻሉትን እና አማካይ ክፍሉ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉትን ኢትዮጵያ ቡናዎች በሽግግር የጨዋታ መንገድ በተሻጋሪ ኳሶች ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ነብሮቹ 18ኛው ደቂቃ ላይ የኋላሸት ሠለሞን ከቡና ተጫዋቾች ጋር ታግሎ ያገኛትን ኳስ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ ወደ ግብ ሲመታው የግብ ዘቡ እስራኤል መስፍን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ቡድኑን ወደ አቻነት አሸጋግሯል።
መጠነኛ መቀዛቀዞች እያስመለከተን በተወሰነ መልኩ ከሚደረጉ ወጥ ያልሆኑ ንክኪዎች በስተቀር ደከም ያለ ቅርፅን የተላበሰው ጨዋታ 36ኛው ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናን መሪ አድርጓል። ራምኬል ጀምስ የግብ ክልሉ ወደ ቀኝ ያመዘነ ቦታ ላይ በየነ ባንጃው ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት የኋላሸት ሠለሞን ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎት አጋማሹ በነብሮቹ 2ለ1 መሪነት ተገባዷል።
ከዕረፍት ተመልሶ በቀጠለው ጨዋታ መጠነኛ መዳከሞች የታዩበት ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚደረጉ ጥረቶችንም በየመሐሉ አስመልክቶናል። ኢትዮጵያ ቡናዎች 55ኛው ደቂቃ ላይ የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ በንክኪ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመግባት የሚደረጉ ሂደቶችን ያስመለከቱን ቢሆንም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚያገኟቸውን ኳሶች ከመጠቀም አንፃር ውስንነቶች ታይቶባቸዋል። በየነ ባንጃው ከርቀት ባደረጋት ሙከራ ወደ ግብ መጠጋት የጀመሩት ሀድያዎች በሽግግር የጨዋታ መንገድ በሚጣሉ ኳሶች የጥቃት ምንጫቸውን ቢያደርጉም ከፊት የነበሩ ተጫዋቾች ግን ስል አልነበሩም።
ጨዋታው 66ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ እስራኤል መስፍን ከግብ ክልል ውጪ ኳስን በእጅ ነክተሃል በሚል በዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛ ወጋየሁ አየለ ጥቆማ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩት ግለቱ ከፍ እያለ በመጣው የቡድኖቹ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በድግግሞሽ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ብናስተውልም ከአጨራረስ አንፃር ግን ድክመቶች ነበረባቸው። 89ኛው ደቂቃ ላይ በሀድያ በኩል የኋላሸት ሠለሞን 90+2 ላይ ደግሞ ፀጋአብ ጋሻው ያለቀላቸውን አጋጣሚዎችን ሞክረው ግብ ጠባቂው ዳዊት ባህሩ አከታትሎ ካዳናቸው በኋላ ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።