የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ለአስራ ስድስቱ የሊጉ ክለቦች በየደረጃቸው የሚሰጣቸው የገንዘብ ሽልማት ምን ያህል እንደሆነ አጣርተናል።
የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ባለንበት ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ይታወቃል። እስከ 28 እና 29ኛው የጨዋታ ሳምንት ድረስ ወራጆቹን ክለቦች ሳይለይ የዘለቀው ሊጉ በጠቀስናቸው የጨዋታ ሳምንታት በቅደም ተከተል ሀምበርቾ እና ሻሸመኔን ወደ መጡበት የከፍተኛ ሊግ ልኮ በላይኛው የዋንጫ ፉክክር ግን አጓጊነቱን ቀጥሎ መደረግ ይዟል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል መካከል ያለው የዋንጫው ዕድል ቅዳሜ በተመሳሳይ ሰዓት 10 ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ እና ሰው ሰራሽ ስታዲየሞች በሚደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ይወሰናል። “የሊጉን ዋንጫ ማን ያገኛል?” ከሚለው የብዙሃን ጥያቄ አዘል ሀሳብ ውጪ ደግሞ የዋንጫ ተፎካካሪዎቹን ጨምሮ ቀሪዎቹ 14 የሊጉ ክለቦች የውድድር ዓመቱን ባጠናቀቁበት የደረጃ ሰንጠረዥ መሠረት እንደ አለፉት ዓመታት የሚሰጣቸው የገንዘብ መጠን ስንት ነው ብለን ለማጣራት ሞክረናል። ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝን አግኝተን ስለገንዘብ ክፍፍሉ ላነሳንላቸው ጥያቄ ተከታዩን ማብራሪያ ሰተውናል።
“በዘንድሮው የውድድር ዓመት በጠቅላላ ጉባዔ ተሻሽለው ከሚተገበሩ ተግባራት አንዱ ለክለቦች በየደረጃቸው የሚከፈለው ክፍያ ማሻሻያ መደረጉ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው ክለቦች በየደረጃቸው ያገኙት የነበረው ክፍያ ልዩነቱ በመቶ ሺዎች እና የተጠጋጋ ነበር ፤ ለዚህም ሌላ የውድድሩን ፉክክር የተሻለ የሚያደርግ ሬሺዎ እና አዲስ ፐርሰንት መሠራት ነበረበት። በተለይምም ከቀጥታ ስርጭት ይከፈል የነበረው 25% የሜሪት ክፍያ ላይ ማሻሻያ ተደርጎበታል። ሌላው 50% እና የፋሲሊቲ እኩል ለክለቦች የሚከፈል ይሆናል። ይህም ማለት አንደኛ የወጣው ክለብ ሌሎቹ እኩል የሚከፈሉ የፋሲሊቲ ክፍያዎችን ሳይጨምር በሜሪት በደረጃ ያገኝ የነበረው ወደ 9.7 ሚሊዮን ያድጋል። ስለዚህ እያንዳንዱ ልዩነት እስከ 1.3 ሚሊዮን ያድጋል ማለት ነው። ስለዚህ ያለው ሬንጅ ሰፊ ይሆናል አንደኛ የሚወጣው ክለብ እና መጨረሻ የሚወጣ ክለብ የሚያገኙት የብር ክፍፍል ልዩነት በሚሊየኖች ሊሆን ይችላል እና አጠቃላይ ሬንጁ ሰፊ ልዩነት አለው። እያንዳንዱ ጨዋታ በነጥብ ልዩነት የደረጃ ልዩነት የሚያመጣ ከሆነ ክለቡ የሚያገኘው ብርም በዛው ልክ እስከ 1.3 ሚሊዮን ብር ልዩነት አለው ማለት ነው። አንደኛው ከሁለተኛው እያለ በመደዳ ወደታች በጠቅላላ ስናየው ይሄን ያህል ብር ልዩነት አለው እና እያንዳንዱ ጨዋታ ለክለቡ ከሚያስገኘው ብር አንጻር ቀላል የሚባል አይደለም።” ያሉን አቶ ሙሉጌታ አስራ ስድስቱ ክለቦች የሚያገኙትን የገንዘበ መጠን ከመዘርዘራቸው በፊት ዝርዝሩ እኩል ክፍፍል 50 ፐርሠንት እና 10 ፐርሠንት ፋሲሊቲ ክፍፍል አያካትትም ብለውን የሁለቱ ክፍያ ሲጨመር አንደኛ የወጣው 18 ሚሊየን ብር እንዲሁም መጨረሻ የወጣው እስከ 8 ሚሊየን ብር ሊያገኝ እንደሚችል አመላክተዋል።
1ኛ 9,746,447.04
2ኛ 8,564,472.35
3ኛ 7,460,004.20
4ኛ 6,433,042.58
5ኛ 5,483,587.50
6ኛ 4,611,638.96
7ኛ 3,817,196.95
8ኛ 3,100,261.48
9ኛ 2,460,832.55
10ኛ 1,898,910.16
11ኛ 1,414,494.30
12ኛ 1,007,584.98
13ኛ 678,182.20
14ኛ 426,285.95
15ኛ 251,896.25
16ኛ 155,013.07
* ይህ የገንዘብ መጠን ክለቦቹ እኩል የሚያገኙትን የተወዳደሩበት እንዲሁም የፋሲሊቲ ክፍያ አያካትትም።