ቅዱስ ጊዮርጊስ ፋሲል ከነማን 4ለ0 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ቋጭቷል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ፈረሰኞቹ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1-1 ከተለያዩበት አሰላለፍ በጨዋታው ዕለት ግብ አስቆጥሮ ፣ ጉዳት አስተናግዶ በወጣው ፍሪምፖንግ ክዋሜ ምትክ አሸናፊ ሞሼን ሲያስገቡ ከወላይታ ድቻ ጋር 0-0 ተለያይተው የመጡት ፋሲሎች በአንጻሩ ሀቢብ መሐመድ ፣ አቤል እያዩ ፣ ዓለምብርሃን ይግዛው እና ፍቃዱ ዓለሙን አስወጥተው ዳንኤል ፍጹም ፣ ኢዮብ ማቲያስ ፣ ብሩክ አማኑኤል እና ቃልኪዳን ዘላለምን አስገብተዋል።
9 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የተጠበቀውን ያህል ፉክክር አልተደረገበትም ነበር። ሆኖም በየጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት የሚቀያየር የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በሁለቱም በኩል ሲያስመለክተን በዐፄዎቹ በኩል ቃልኪዳን ዘላለም እና ምኞት ደበበ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።
በመጠኑ በተነቃቁት የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ ተጭነው መጫወት ሲችሉ 43ኛው ደቂቃ ላይ ተገኑ ተሾመ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት ተፈራ በጥሩ ዕይታ በግራ መስመር ለተገኘው ለየአብሥራ ተስፋዬ ያሻገረለትን ወጣቱ ተጫዋች ተከላካዮችን ጭምር አልፎ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መትቶ ኳሷ የግቡ አግዳሚ ብረትን ገጭታ ወጥታለች።
ጨዋታው 45ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ጎል ተቆጥሮበታል። አሸናፊ ሞሼ ከመሐል እየገፋ የሄደውን ኳስ ወደ ቀኝ ለተገኑ ሰጥቶት ተጫዋቹ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ዳዊት ተፈራ አቀብሎት ከሳጥኑ ጠርዝ ሳማኪ ሚኬል መረብ ላይ ግሩም ግብ አሳርፎ ፈረሰኞቹን መሪ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት ተሻሽሎ ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊሶች 48ኛው ደቂቃ ላይ በሻሂዱ ሙስጠፋ 50ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በዳዊት ተፈራ የቅጣት ምት ያደረጓቸውን ሙከራዎች ግብ ጠባቂው ሳማኬ ሚኬል ሳይቸገር መልሷቸዋል።
ኢዮብ ማቲያስን አስወጥተው ሸምሰዲን መሐመድን በማስገባት ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ዐፄዎቹ 51ኛው ደቂቃ ላይ በሸምሰዲን መሐመድ አማካኝነት ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም በግቡ አግዳሚ ሲወጣባቸው ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
በማያቋርጥ ሽግግር ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች 53ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው የአብሥራ ተስፋዬ ከዳዊት ተፈራ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ወደ ውስጥ ቀንሶት ዳግማዊ አርዓያ ወርቃማውን ዕድል አባክኖታል።
ፋሲል ከነማዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ በጌታነህ ከበደ ከረጅም ርቀት ሙከራ ካደረጉ በኋላ ባልተደራጀው እንቅስቃሴያቸው 67ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊቆጠርባቸው ተቃርበው ዳግማዊ አርዓያ የግብ ጠባቂውን ሚኬል ሳማኬን መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ የመታው ኳስ ነጥሮ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ፈረሰኞቹ በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ፍጹም ብልጫ ሲወስዱ 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ኤርቦ ከመሃል በተሻገረለት ኳስ የሳማኬ ሚኬልን ደካማ የጊዜ አጠባበቅ ውሳኔ ተመልክቶ ከፍ አድርጎ ጎል ማስቆጠር ሲችል 90+1ኛው ደቂቃ ላይም ራሱ አማኑኤል ከዳዊት ተፈራ የተቀበለውን ኳስ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ጎል ማስቆጠር ሲችል 90+5ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተገኑ ተሾመ ከአላዛር ሳሙኤል በተቀበለው ኳስ ግብ ጠባቂውን ሳማኬን ጭምር አታልሎ በማለፍ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የፋሲል ከነማው ምክትል አሰልጣኝ ሙሉቀን አቡሃይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንደነበሩ ሆኖም ግን የመከላከል አደረጃጀታቸው ጠንካራ እንዳልነበር ተናግረው የማያስደስት ውጤት እንደሆነ ጠቁመው የዛሬው የ4ለ0 ሽንፈት የውድድር ዓመቱን እንቅስቃሴያቸውን እንደማይገልጽ እና በሚቀጥለው ዓመት ተሻሽለው እንደሚቀርቡ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ በበኩላቸው ተጫዋቾቻቸው ልምምድ ላይ የተነገራቸውን ነገር በመተግበራቸው ደስተኛ እንደሆኑ ሲገልጹ በውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች ታዳጊዎችን ማየታቸውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ጠቅሰው ለቀጣይ ዓመት ከልምዳቸው አንጻር ተሻሽለው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።