ሪፖርት | ሲዳማ ቡናዎች ዓመቱን በሽንፈት ጀምረው በድል አጠናቀዋል

ሲዳማ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ ይገዙ ቦጋለ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ተከታታይ ሁለተኛ ድላቸውን አስመዝግበው ዓመቱን በድል አጠናቀዋል።

ከድል የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች ከባለፈው ስብስባቸው ግብ ጠባቂያቸውን መክብብ ደገፉን በግብ ጠባቂ መስፍን ሙዜ ብቻ ሲቀይሩ በአንጻሩ ከሀዋሳ ጋር 1-1 ተለያይተው የመጡት የጣና ሞገዶቹ አላዛር ማርቆስ ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ ዓባይነህ ፊኖ እና ሐብታሙ ታደሰን አስወጥተው ይገርማል መኳንንት ፣ አብዱላዚዝ ሲያሆኔ ፣ በረከት ጥጋቡ እና ፍሬው ሰለሞንን አስገብተዋል።


አስራ ዘጠነኛ ጨዋታቸውን በመሩት ኢንተርናሽናል አልቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ በተመራው በዚህ ጨዋታ ነቃ ባለ ፉክክር የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ ገና ጨዋታው በተጀመረው በ20ኛው ሰከንድ የተመዘገበ ነበር። በፍጥነት ታግለው ሰብረው የገቡት ባህር ዳሮች ወንደሰን በለጠ ሳጥን ውስጥ በመግባት የላከውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን የግቡ አግዳሚ ጎል እንዳይሆን ከልክሎታል።

ታዲያ በዚህ ሙከራ በጀመረው ጨዋታ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች መሪ መሆን ችለዋል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ፈጥነው የወጡት ሲዳማዎች ከደስታ ዮሐንስ የተላከለትን ማይክል ኪፕሩቪ የተሰጠውን ሰንጣቂ ኳስ ጉልበቱን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ ሲገባ በተከላካዮች የተደረበውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ከጠባብ አንግል በአስደናቂ አጨራረስ የቡድኑን ቀዳሚ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

የሲዳማን ፈጣን የማጥቃት አጀማመርን ለመቆጣጠር የተቸገሩት የጣና ሞገዶቹ ከሦስት ደቂቃ በኋላ ተከላካዮቹ በፈጠሩት የአቋቋም ችግር ምክንያት ባህር ዳሮች ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። ከፍቅረኢየሱስ ተክለብርሃን መነሻውን ያደረገው የማጥቃት ሂደት በቀኝ መስመር ቡልቻ ሹራ ኳሱን ተቀብሎ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን ይገዙ ቦጋለ በግንባሩ በመግጨት ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

በ19ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ቡልቻ ሹራ ኳሱን በጥሩ ሩጫ ከተቆጣጠረ በኋላ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም በደካማ አጨራረስ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል መሆን የሚችለውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመሪያው 20 ሴኮንድ ካደረጉት አደገኛ ሙከራ በኋላ ሌላ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ቢሆንም በጨዋታው እንቅስቃሴ ውስጥ ለመቆየት ኳሱን ተረጋግተው ለመጫወት ጥረቶች ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህ ሂደትም በአጋማሹ መጠናቀቂያ 42ኛው ደቂቃ ላይ የአብሥራ ተስፋዬ ነጻ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም
ኳሱን በቀላሉ ለግብ ጠባቂው መስፍን አሳቅፎታል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ከሁለት ተከላካይ አማካይ ፍቅረሚካኤልን በመቀነስ ፀጋዬ አበራን በማስገባት የማጥቃት አቅማቸውን ለማሳደግ ያደረጉት ጥረት እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በተመሳሳይ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል በሚኖር የውሳኔ ችግር እና የሲዳማ ተከላካዮችን አስከፍቶ ለመግባት ውስንነት ነበረባቸው። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በፈጣን እንቅስቃሴ መቀጠል ባልቻለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 68ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ ያገኙት ፍጹም ቅጣት ምት ጨዋታውን አነቃቅቶታል። ደስታ ደሙ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ፍጹም ጥላሁን ወደ ጎልነት
በመቀየር ባህር ዳርን ወደ ጨዋታው ማስገባት ችሏል።

ወደ አቻነት ለመግባት የተሻለ ፍላጎት ያሳዩት ባህር ዳር ከተማዎች በተደጋጋሚ ጎል ፍለጋ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይም በ75ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከሳጥን ውጭ በቀጥታ የመታውን ግብ ጠባቂው መስፍን ሙዜ እንደምን ያወጣበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በእጃቸው የገባውን ነጥብ ለማስጠበቅ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው በመከላከል ሥራ ላይ ያተኮሩት ሲዳማ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት ሽግግር ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ባይፈጥሩም ባህር ዳር ላይ ጫና ሲያሳድሩ የነበረበት ዕቅዳቸው ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዓመቱን በድል አጠናቀዋል።


የባህር ዳር ከተማ ምክትል አሰልጣኝ መብራቱ ሀብቱ በሰጡት አስተያየት በተጋጣሚ ፈጣን ሽግግር በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ይዘውት የመጡትን ታክቲክ እንዳይተገብሩ ቢያደርጋቸውም ከዕረፍት መልስ ለማስተካከል ጥረት እንዳደረጉ ተናግረው ከዓምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅድው የነበረ ቢሆንም የተለያዩ አስቸጋሪ የሆኑ ጊዜያትን እንዳሳለፉ እና የነበረው ችግርን ተጋፍጠው የተሻለ ውጤት ይዘው እንደጨረሱ አስረድተው በቀጣይ ዓመት በተሻለ መንገድ ጥሩ የሆነውን ባህር ዳር ለመገንባት ከወዲሁ ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመዋል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በበኩላቸው አርባ ነጥብ ይዘው ለመጨረስ ከክለቡ ጋር ዕቅድ እንደነበራቸው ተናግረው ይህን በማሳካታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ ዓመት በውድድር ብቻ ሳይሆን ተተኪ ተጨዋቾችን በማፍራት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ እና ጠንካራ ተፎካካሪ የዋንጫ ቡድን እንደሚሠሩ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።