ዘሪሁን ሸንገታ ወደ አዲሱ የሊጉ ክለብ?

ዘሪሁን ሸንገታ በተጫዋችነት እና በአሠልጣኝነት በብቸኝነት ካገለገለበት የፈረሰኞቹ ቤት ከተለያየ በኋላ ወደ አዲስ ክለብ ለማምራት ከጫፍ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ረጅም የተጫዋችነት እና የአሰልጣኝነት ቆይታ የነበረው ዘሪሁን ሸንገታ በተጠናቀቀው የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ23ኛ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ቡድኑ ከተሸነፈ በኋላ ከመንበሩ በጊዜያዊነት እንዲታገድ መደረጉ አይዘነጋም። አሠልጣኙ ከክለቡ ጋር ያለው እህል ውሀ በምን መልኩ ይጓዛል የሚለው ጉዳይ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም አብዛኛውን የተጫዋችነት እና የአሠልጣኝነት ህይወቱን ካሳለፈበት ቅዱስ ጊዮርጊስ በመለያየት ወደ ሌላ የሊጉ ክለብ ለማምራት ስምምነት ላይ እንደደረሰ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካሳደገው አሠልጣኝ ሳምሶን አየለ ጋር የተለያየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቦታው ዘሪሁንን ለመሾም ከጫፍ ስለመድረሱ ተረጋግጧል። ሶከር ኢትዮጵያ ከምንጮቿ ባረጋገጠችው መሠረት ክለቡ ከሳምሶን ጋር እንደማይቀጥል ከወሰነ በኋላ በዋናነት ከሁለት አሠልጣኞች ጋር ንግግር አድርጎ ከዘሪሁን ጋር ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሷል። ሹመቱም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።