በሊጉ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች ሜዳሊያ ይሸለማሉ?

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የኮምኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ በሊጉ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦችን የሜዳሊያ ሽልማት በተመለከተ ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የዘንድሮውን ዓመት ፍልሚያ በነገው ዕለት እንደሚፈፅም ይታወቃል። ቀልቦች ሁሉ በዋንጫው ፉክክር ላይ የሚገኙ ሲሆን ከመቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንዱ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ እንደሌሎቹ ክለቦች ከሚያገኙት የገንዘብ ሽልማት ውጪ እንደ ዓምናው የሜዳሊያ ተሸላሚ የመሆናቸውን ጉዳይ በተመለከተ የዝግጅት ክፍላችን ማጣራት አከናውናለች። በዚህም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የኮምኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ጉዳዩን በተመለከተ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል።

“በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላለመውረድም ሆነ ዋንጫ ለማንሳት የነበረው ፉክክር ጠንካራ የውድድር ዓመት ያየንበት ነው ማለት ይቻላል። እስከ 28ኛ እና 29ኛ ሳምንት ድረስ ወራጁ ያልተለየበት ዓመት አሳልፈናል ፤ እንዲሁም ለዋንጫ የሚደረገው ፉክክር ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን አንስተው የማያውቁ ክለቦች በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ ቆይታ እያደረጉ ነው። በአንድ ነጥብ ልዩነት ላይ እንዳሉ ይታወቃል ፤ እንግዲህ ለ2016 ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚደረገው ትግል ለ1 ዋንጫ እና ለ45 የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ብቻ ነው።” ያሉን አቶ ሙሉጌታ እንዳለፉት ዓመታት ሁለተኛ እና ሦስተኛ የወጡ ክለቦች የብር እና የነሀስ ሜዳሊያ በዚህኛው ዓመት የማያገኙበትን ምክንያት በቀጣይ ማስረዳት ይዘዋል።

“ከዚህ በፊት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ለወጡ ክለቦች ይሰጥ የነበረው የብር ሜዳልያ እና የነሃስ ሜዳልያ በዚህኛው የውድድር ዓመት የለም። ይኸውም ከዚህ በፊት ሁለተኛ የወጣው ክለብ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ይሳተፍ ስለነበር የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ላይ እንደሚያገኘው ሽልማት ሁሉ ሁለተኛነት የብር ሜዳልያ ቢሰጠው እንዲሁም በውድድሩ ሦስተኛ ያጠናቀቀው የነሃስ ሜዳልያ ቢሰጠው በሚል ስናካሂደው ቆይተናል ፤ አሁን ግን የኢትዮጵያ ዋንጫ የተዘጋጀ ስለሆነ እንዲሁም ከአንድ ፕሪሚየር ሊግ አንጻር ሁሉም ክለቦች ሊታገሉ የሚገባው ለአንድ ዋንጫ እና ዋንጫውን ተከትሎ ለሚሰጡ ሜዳልያዎች መሆን አለበት በሚል ዋንጫ ለሚያገኘው ክለብ ብቻ አንድ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እና 45 ሜዳልያዎች ተዘጋጅተዋል። ይህ ትግልም በክለቦች መካከል ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለን እናምናለን ፤ ይህም በውድድር ደንቡ ላይ ሰፍሮ እየተተገበረ ይገኛል።” ብለዋል።

ነገ ፍፃሜውን የሚያገኘው ውድድሩ እኩል 10 ሰዓት በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም እንዲሁም በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ውዱ ዋንጫ እና 45ቱ ሜዳሊያዎች መዳረሻቸውን ያገኛሉ። የነገ ጨዋታዎችን በተመለከተም የሊጉ አስተዳደር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዳደረገ የኮምኒኬሽን ኃላፊው ይጠቁማሉ።

“በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሁለት ሳምንት ውድድሮች የክለቦችን ውጤት ታሳቢ በማድረግ ጨዋታዎች በሁለት ሜዳ ላይ ይደረጋሉ። ላለመውረድም ሆነ ዋንጫ ለማንሳት ባለው ሂደት ውስጥ የቶርናመንት ውድድራችንን በምናካሂድበት ወቅት ላይ ሌሎች አማራጭ ሜዳዎችን በመፈለግ የክለቦችን ውጤት ታሳቢ በማድረግ በሁለት ሜዳዎች ውድድሮችን እናደርጋለን። አሁንም በ29ኛው እና በ30ኛው ሳምንት እያደረግን ያለነው ይህንን ነው። አሁን ላይ በ30ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመጨረሻው ሳምንት ማለት ነው በአንድ ነጥብ ልዩነት ሁለት ክለቦች ለዋንጫ ተፋጠዋል። ስለዚህ ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት የተሻለ ነጥብ ያለው የተሻለ የሜዳ ዕድል እና የቀጥታ ስርጭት ያገኛል በሚለው ጨዋታዎቹ በሁለቱ ሜዳዎች ተደልድለዋል። ኢትዮጵያ መድንን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያገናኘው ጨዋታ ውድድሩ በዋናነት ሲካሄድበት በነበረው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እና የቀጥታ ስርጭቱ ባለበት ይደረጋል። ሁለተኛው መቻልን ከድሬዳዋ ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ በሀዋሳ ሰው ሠራሽ ሜዳ የሚደረግ ይሆናል ማለት ነው።

“በዋንጫ እና በሴርሞኒ ደረጃ የተዘጋጀው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ነው። ነገር ግን ዋንጫውን ማን እንደሚያነሳ ስለማይታወቅ የዋንጫ ሴርሞኒው የሚደረገው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይሆናል ማለት ነው በዛውም የቀጥታ ስርጭት ባለበት ፤ ሁለተኛው ቡድን ዋንጫውን የማንሳት ዕድል ካለው ወደዚህኛው ሜዳ ተጉዞ ሴርሞኒው ላይ የሚካፈል ይሆናል ማለት ነው። ውድድሮቹ በተመሳሳይ 10 ሰዓት ላይ ይደረጋሉ። ቀጣይ ያለው ሴርሞኒ ግን ከ20 ደቂቃ በኋላ የሚኖረው የዋንጫ ስርዓት ፕሮግራም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል ማለት ነው።” ብለውናል።