ዛሬ የቁርጥ ቀን ነው ፤ የመጨረሻው ዕለት። የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል በየፊናቸው ዕድላቸውን ይሞክራሉ። ከሁለቱ ወሳኝ ጨዋታዎች በፊት በቡድኖቹ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን እንደሚከተለው አጠናክረናል።
የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር እስከ ትናንት ድረስ 238 ጨዋታዎችን አከናውኖ በዛሬው ዕለት ለመጠናቀቅ የሁለት 90 ደቂቃዎች የጨዋታ ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። በወቅታዊነት የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ አናት የተቆናጠጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ከኢትዮጵያ መድን ጋር ሲፋለም በተመሳሳይ ሰዓት በሀዋሳ አርቴፊሻል ሳር ስታዲየም ደግሞ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኝነት የተቀመጠው መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ይጋጠማል።
በአሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ባንክ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ዕድል ይዞ ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን በጨዋታውም አጥቂው ሳይመን ፒተርን በቅጣት ከማጣት ውጪ ሁሉንም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚያገኝ ተጠቁሟል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ተከላካዩ ሚሊዮን ሠለሞን ወደ አሜሪካ በማምራቱ የወሳኙን ተጫዋች ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን አምበሉ አብዱልከሪም መሐመድ ግን ከቅጣት መልስ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደገበት ዓመት የሊጉን ክብር ለማሳካት ከኢትዮጵያ መድን ለሚጠብቀው ወሳኝ ጨዋታ በርካታ ደጋፊዎቹ በስታዲየሙ እንደሚታደሙለት ይጠበቃል። ክለቡ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ያልተለዩት ደጋፊዎች ላቅ ባለ ቁጥር በሀዋሰ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ታድመው ቡድናቸውን ለማበረታታት ዝግጅት ስለመቋጨታቸው ተሰምቷል። በሀዋሳ የሚገኙ ነዋሪዎች ቡድኑን እንዲደግፉለት የማስ ስፖርት መርሀግብርን ዛሬ ማለዳ ያሰናዳው ክለቡ በከተማዋ እና በዙሪያዋ እንዲሁም በአቅራቢዋ ካሉ ከተሞች የሚገኙ የባንኩ ሰራተኞች እና የበላይ አመራሮችን እንዲሁም ደግሞ ሌሎች ግለሰቦች የመጨረሻዋን የስኬት ጎዳና በድል ለመወጣት ከጎኑ እንዲቆሙ ወደ አስር ሺህ የሚጠጉ ደጋፊዎችን እንዳዘጋጀ ተነግሯል ፤ በክለቡ ታቅፈው የሚገኙ የአትሌቲክስ እና መሠል ስፖርቶች ተሳታፊ አባላቱንም ክለቡ በመያዝ ሀዋሳ ከተማ ከትሟል።
ይህንን ወሳኝ ጨዋታ ፌድራል ዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ በመሐል ዳኝነት ሲመሩት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሙሉነህ በዳዳ ረዳቶች በረዳትነት እንዲሁም ሔኖክ አበበ በአራተኛ ዳኝነት ግልጋሎት እንደሚሰጡ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በበኩሉ የ80ኛ ዓመት ክብረ-በዓሉን በዋንጫ ለማጣጣም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መሸነፍ አልያም ነጥብ መጣል እያሰበ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ለመርታት እና ለመርታት ወደ ሜዳ ይገባል። በ29ኛ ሳምንት ከነዓን ማርክነህን በቅጣት አጥቶ የነበረው ቡድኑ ወሳኙን ተጫዋች ዛሬ የሚያገኝ ሲሆን አንድም ተጫዋች በጉዳትም በቅጣትም ከስብስቡ እንዳልወጣበት ሰምተናል። የመቻል ተጋጣሚ ድሬዳዋ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ዛሬ አያገኝም። በዚህም በጉዳት እና በግል ጉዳይ ዳንኤል ተሾመ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ አብዱለጢፍ መሐመድ ፣ መሐመድ አብዱልጋኒዮ ፣ ያሬድ ታደሠ ፣ ዘርአይ ገብረስላሴ ፣ አቤል አሰበ እና ኤፍሬም አሻሞ ግልጋሎት አይሰጡም።
የሊጉን የዋንጫ ታሪክ ለመቀላቀል ከንግድ ባንክ በአንድ ነጥብ አንሶ የተቀመጠው መቻል በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ ድሬዳዋ ከተማን በሞት ሽረት መርሀግብር ያስተናግዳል። ቡድኑ የንግድ ባንክን ነጥብ መጣል እየጠበቀ ዓመቱን በድል አጅቦ ለማጠናቀቅ በርካታ ደጋፊዎቹን ይዞ ሀዋሳ ደርሷል። በመቻል ስፖርት ክለብ ስር ያሉ የአትሌቲክስ ፣ ቦክስ እና የታዳጊ እግር ኳስ ቡድን አባላቱ እንዲደግፉለት ሀዋሳ ይዞ የተገኘው ክለቡ በተጨማሪም ከተለያዩ የመከላከያ የጦር ካምፕ እና ዕዞች ከስምንት ሺህ በላይ ደጋፊዎችን ያቀፈ ሲሆን በጥዑም የማርሽ ባንዱ እየታጀበ በድሬዳዋው ጨዋታ የመጨረሻ ፍልሚያውን ያከውናል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህንን ጨዋታ ደግሞ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ አራተኛ ዳኛ ሆነው እንዲመሩ ተመድበዋል።