እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ በፉክክር የዘለቀው የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ መድኖች በ29ኛው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን 1ለ0 ከረቱበት አሰላለፍ ዋንጫ ቱት እና አሚር ሙደሲርን አስወጥተው አብዱልከሪም መሐመድ እና ንጋቱ ገ/ሥላሴን ሲያስገቡ ባንኮቹ በአንጻሩ ሻሸመኔን 2ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ ሐብታሙ ሸዋለምን አሳርፈው ብሩክ እንዳለን አስገብተዋል።
10፡00 ሲል ሪከርድ በሆነ የተመልካቾች ብዛት ታጅቦ በፌዴራል ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ገና በሦስተኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ፈቱዲን ጀማል በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ኪቲካ ጅማ ለሱሌይማን ሐሚድ አመቻችቶ ሰጥቶት ሱሌይማን አክርሮ የመታው ኳስ በንጋቱ ገ/ሥላሴ ተጨርፎ መረቡ ላይ አርፏል።
ኢትዮጵያ መድኖች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ተጭነው መጫወት ቢችሉም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 33ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ሐይደር ሸረፋ ለማቀበል የሞከረውን ኳስ አዲስ ግደይ በግንባር ገጭቶ ከመለሰው በኋላ ያገኘው ባሲሩ ኦማር መልሶ አቃብሎት አዲስም እጂግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ከሳጥን ውጪ በመምታት በውድድሩ ከታዩ ድንቅ ጎሎች አንዱ አድርጎታል።
ባንኮች መሪነታቸውን በሁለት ጎል ልዩነት ካደረጉ በኋላ በራስ መተማመናቸውን ጨምረው መጫወታቸውን ሲቀጥሉ ባንጻሩ ኢትዮጵያ መድኖች 40ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን ፈጥረው ወገኔ ገዛኸኝ ከአለን ካይዋ በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥን ጠርዝ ላይ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አስወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ባሲሩ ኦማር 68ኛው ደቂቃ ላይ ከአዲስ ግደይ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን ጠርዝ ሞክሮት በግቡ የቀኝ ቋሚ የወጣበት ኳስ ብቻ ተጠቃሽ ነበር። ኢትዮጵያ መድኖች በጥሩ የኳስ ቁጥጥር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተደራጅተው ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም ወደ ራሳቸው ተጠግተው ለመጫወት የመረጡትን ንግድ ባንኮችን አልፈው ለመግባት ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ጨዋታው 2ለ0 መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ወደ ፕሪሚየር ሊግ ባደጉበት ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን አንስተዋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቀድሞ በተቆጠረባው ጎል መረጋጋት አለመቻላቸውን ጠቁመው ከመድን ለቀው ንግድ ባንክን የተቀላቀሉት ሐብታሙ ሸዋለም ፣ ባሲሩ ኦማር እና ሳይመን ፒተር በቡድኑ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው ሲናገሩ የቻምፒዮኑ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው ጭንቀት እንደነበረባቸው ጠቁመው ዋንጫ እንደሚያነሱ ግን እርግጠኞች እንደነበሩ እና ቻምፒዮን መሆናቸው ለወደፊቱ መነሳሻ እንደሚሆናቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።