ምዓም አናብስት የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ለመፈፀም ከጫፍ ደርሰዋል።
በአስከፊው ጦርነት ምክንያት ለዓመታት ከእግር ኳሳዊ እንቅስቃሴ ውጭ ሆነው ከቆዩ በኋላ በዘንድሮ የውድድር ዓመት የትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባዘጋጀው ውድድር ሲሳተፉ በመቆየት የሊጉን ዋንጫ ያነሱት ምዓም አናብስት ከዓመታት በኋላ የሚመለሱበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ አስቀድሞ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር መቃረባቸው ታውቋል። ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ታማኝ ምንጮች እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የውድድር ዓመቱን የመቻል ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ ሲሰራ የቆየው ዳንኤል ፀሀዬ ቡድኑን ለመረከብ መቃረቡን ማረጋገጥ ችላለች። ከሰኔ 11 ጀምሮ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የቆዩት መቐለዎች ሦስት እጩዎች ሲያወዳድሩ ከቆዩ በኋላ በስተመጨረሻም ዳንኤል ፀሀዬን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድገው ለመሾም ከጫፍ ደርሰዋል።
በርካታ ወጣት ተጫዋቾች ባፈራው የደደቢት ወጣት ቡድን ከጀመረው የአሰልጣኝነት ሂወቱ በኋላ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝነት እንዲሁም ስሑል ሽረን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳደግ የቻለው አሰልጣኙ በፕሪምየር ሊጉ በደደቢትና በከፍተኛ ሊጉ አክሱም ከተማ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ መስራቱ ሲታወስ አሁን ደግሞ ለአንድ የውድድር ዓመት ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ ከሰራበትና እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ የዋንጫ ተፎካካሪ ከነበረው መቻል ተለያይቶ ምዓም አናብስትን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት ከጫፍ ደርሷል።
በዘጠናዎቹ ጎልተው ከወጡ ኮከቦች አንዱ የሆነው ዳንኤል ፀሀዬ ከ1987 እስከ 1999 በዘለቀው የእግር ኳስ ሂወቱ አስራ አንድ ዓመታት የተጫወተበትና “እንደ እናቴ ቤት ነው የማየው” ከሚለው ጉና ንግድና አዳማ ከተማ እንዲሁም በሦስት የዕድሜ ዕርከኖች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫውቶ አሳልፏል። በተጫዋችነት ሂወቱ ከቁመቱ በላይ ዘሎ በሚያስቆጥራቸው ጎሎች፤ በአክሮባቲክ የደስታ አገላለፁና ስዊድን ላይ በደርሶ መልስ ባስቆጠራቸው ግቦች የሚታወሰው የቀድሞ አጥቂ ከቀረቡት የመጨረሻ ዕጩዎች ውስጥ ለፕሪምየር ሊጉ አሁናዊ ሁኔታ ያለው የተሻለ ቅርበት ተመራጭ እንዳደረገውም ታውቋል።