የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሆነው መስፍን ታፈሠ በቀጣዩ አርብ ለሙከራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናል።
ከሀዋሳ የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች በተነሳው የእግር ኳስ ህይወቱ በ2011 መጋቢት ወር ላይ የክለቡ ዋናውን ቡድን በመቀላቀል ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጋር መተዋወቅ የቻለው መስፍን ታፈሰ በአሳዳጊ ክለቡ ከታዳጊ ቡድን አንስቶ የስድስት ዓመታት ቆይታ ማድረጉ ይታወሳል። በመቀጠል በ2015 ወደ ኢትዮጵያ ቡና በማምራት በክለቡ ግልጋሎት እየሰጠ ውሉ በያዝነው ወር የሚያበቃው ተጫዋቹ ለሙከራ ወደ ደቡብ አፍሪካ የፊታችን አርብ ሐምሌ 5 እንደሚያቀና ወኪሉ አዛርያስ ተስፋፂሆን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።
ማሜሎዲሰንዳውስ ሻምፒዮን በሆነበት የዘንድሮው የደቡብ አፍሪካው አብሳ ፕሪምየር ሺፕ በ39 ነጥቦች 8ኛ ደረጃን በመያዝ የቋጨው ፖሎኩዋኔ ሲቲ መስፍን ታፈሠን ለሙከራ የጋበዘው ክለብ ሆኗል። አስራ ስድስት ክለቦች በሚሳተፉበት የሀገሪቱ ትልቁ ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው እና ከተመሠረተም ሀያ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የአሰልጣኝ ፑቲ ጆንሰኑ ክለብ ኢትዮጵያዊው አጥቂ የአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜ እንደሚኖረው ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች።