​’አሮን ሲማግሊቼላ’ ይሄንን ስም አስታውሱት!

ዘ ጋርድያን ከምርጥ ስልሣ ወጣት ተጫዋቾች ውስጥ ያካተተው “አዲሱ ኮርማ”

ባለፉት ጊዜያት በባየርን ሙዩኒክ ወጣት ቡድን የሚገኘው ልኡል ብሩክ ፤ በቪያሪያልና የስፔን ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝው ኦስካር ሽመልስ፤ በቀጣይ የውድድር ዓመት የዩዲኔዜ ዋናው ቡድን አካል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው እንድሪስ ስካራሜሊ፤ የውድድር ዓመቱን በውሰት ከፌይኖርድ ሮተርዳም ታዳጊ ቡድን ጋር ያሳለፈው ይስሀቅ አለማየሁና ሌሎች በርከት ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማስተዋወቃችን ይታወሳል፤ ለዛሬ ደግሞ  በጣልያን እግር ኳስ ትኩረት ከሳቡ ወጣት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ልናስተዋውቃቹ ወደናል።

ሙሉ ስሙ አሮን ሲማግሊቼላ ይባላል፤ የቱሪን ተወላጅ ከሆነች እናቱ ካቲያና ከኢትዮጵያዊው አባቱ ማቲያ አዲሱ ሲማግሊቼላ በቱሪን ከተማ የተወለደው ይህ የአስራ ዘጠኝ ዓመት ተጫዋች ከወዲሁ ትልቅ ትኩረት ስቧል። ከአራት ዓመቱ ጀምሮ የእግር ኳስ ‘ሀ’ ‘ሁ’ ያስተማረችውን የቶሪኖ ንብረት የሆነው ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተሰጥኦ ያለው አማካይ በቶሪኖ አራት የታዳጊ ቡድኖች ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ ዋናው ቡድኑን ተቀላቅሏል። 


ላለፉት ዓመታት ሲወዳደርበት በነበረው Primavera 1 ባሳየው ድንቅ ብቃት ከወዲሁ የበርካታ ቡድኖች ትኩረት የሳበው ወጣቱ አማካይ ለስፖርት ያለውን ፍቅር ባቱ (ዝዋይ) ተወልዶ በሚላን ከተማ በማደጎነት ያደገውን የቀድሞ እግርኳስ ተጫዋች ወላጅ አባቱ መነሻት እንዳገኘው ይናገራል። በሴሪ ዲ እንዲሁም በፉትሳል ክለቦች የተጫወተው ኢትዮጵያዊው ወላጅ አባቱ በአንድ ወቅት ከእውቁ ጣልያናዊ ጋዜጠኛ ጅያንሉካ ዲማርዝዮ ጋር በነበረው ቆይታም “የሁለት ወይም ሶስት ዓመት ልጅ እያለ ሁልጊዜ ኳስ በእጁ ይዞ ሊያየኝ ሜዳ ይመጣ ነበር፤ አስቀድሞ የተወሰነ ዝንባሌ እንደነበረውም ግልጽ ነበር” ብሎ ነበር።

‘ሲማ’ በሚባል የቁልምጫ ስሙ የሚታወቀው ወጣቱ ተጫዋች የላቀ ቴክኒካዊ ችሎታው እንደ አማካኝ፣ አጥቂ እና ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሆኖ እንዲጫወት ያስችለዋል። ምንም እንኳ አማካይ ቢሆንም ግዙፉ ስዊድናዊ አጥቂ እንደ አርአያ እየተከተለ እንዳደገም ይነገርለታል። 

በአሰልጣኝ ፓትሪዚያ ፓኒኮ አማካኝነት ለመጀመርያ ጊዜ በጣሊያን ከ15 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከተጫወተ ወዲህ በሦስት የዕድሜ እርከኖች ሀገሪቱን ያገለገለው ሲማ በ2022 ዘ ጋርድያን በዘረዘራቸው በ2005 የተወለዱ ምርጥ ስልሳ ወጣት ተጫዋቾች ተካቷል፤ በዝርዝሩም ከትውልደ ኢትዮጵያዊው በተጨማሪ የባርሰሎናው ቪክቶር ሮኩ፣ የርያል ማድሪዱ አርዳ ጉሌርና የባየርን ሙዩኒኩ ማትያስ ቴል ተካተው ነበር። ታማኝ የጣሊያን ጋዜጦች እንደገለፁት ከሆነ ፉልሃም የቶሪኖውን ኮከብ የረዥም ጊዜ ፈላጊ ሲሆን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለም ይገኛል።  ሌላው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አማካይ ይስሀቅ አለማየሁን የያዘው ፌይኖርድም አዲሱ ፈላጊ ሆኖ ብቅ ብሏል፤ ሆኖም የጣልያኑ ክለብ በ2025 ውሉን ለሚያበቃው ተጫዋች የማቆየት ፍላጎት እንዳለው ታውቋል። የወጣቶች ቡድን ስራ አስኪያጅ ሩጌሮ ሉደርጋኒ የተጫዋቹን ውል ለማደስ ተስፋ እያደረገ ሲሆን ተጫዋቹ እና ተወካዮቹ ከክለቡ ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ በቀጣይም ስታዲዮ ኦሊምፒኮ ግራንዴ ቶሪኖ እንደሚቆይ ይጠበቃል።

በ Primavera 1 ቆይታው አስራ ሦስት ግቦች አስቆጥሮ ዘጠኝ ግብ የሆኑ ኳሶች ማመቻቸት የቻለው ተስፈኛው ተጫዋች ከዋናው ቡድን ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት ለማድረግ ከኢቫን ጁሪች ጥሪ እንደደረሰውም ታውቋል።