ግዙፉ ሀገር በቀል የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጎፈሬ ኢንተርናሽናል አርቢትር በዓምላክ ተሰማን የኩባንያው አዲሱ የብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን ዛሬ አመሻሽ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደ ስነ-ስርዓት አስታውቋል።
አመሻሽ ላይ በተደረገው መርሃግብር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁንን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዚሁ መርሃ ግብር ሁነቱ ጅማሮውን ያደረገው በጎፈሬ መስራች እና ባለቤት የሆኑት አቶ ሳሙኤል መኮንን በስምምነቱ ዙርያ በሰጡት አስተያየት ነበር።
አቶ ሳሙኤል በንግግራቸው ተቋማቸው በተለያዩ መስኮች ፈርቀዳጅ ስለመሆኑ አንስተው የዛሬው ስምምነትም ከብራንድ አምባሳደርነት ባለፈ ከዳኝነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ያለውን ከፍተኛ የዳኞች ትጥቅ ፍላጎትን ለመቅረፍ የታለመ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በማስከተል መድረኩን የተረከቡት ኢንተርናሽናል አልቢትር በዓምላክ ተሰማ በበኩላቸው ከ15 ዓመታት በላይ በዘለቀው የዳኝነት ህይወታቸው ዳኞች በጨዋታ ወቅት የሚለብሱት ትጥቅ ማግኘት ፈታኝ እንደነበር አንስተው ከጎፈሬ ጋር ከዳኞች ጋር በተያያዘ ያለው መጠነ ሰፊ የትጥቅ ችግሮችን መቅረፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙርያ ላለፉት ሶስት ዓመታት ንግግሮች ሲያደርጉ ስለመቆየታቸው ጠቅሰው ስምምነቱም የዳኞች ትጥቅን ከማቅረብ በዘለለ የሀገራችን የእግር ኳስ ዳኝነት ለማገዝ የታለመ ስለመሆኑ አንስተው የዚህ ታሪካዊ ስምምነት አካል በመሆናቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው አንስተዋል።
በመቀጠል አቶ ሳሙኤል መኮንን እና ኢንተርናሽናል አልቢትር በዓምላክ ተሰማ ለሶስት ዓመታት የሚዘልቀውን ስምምነት በፊርማቸው ያፀኑ ሲሆን ፤ በማስከተልም ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ ተቋም በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረታቸውን እና በተለያዩ አማራጮች ለገበያ የሚቀርቡትን አዳዲስ የዳኛ ትጥቆች እና ሌሎች ቁሶችን የተዋወቁ ሲሆን በማስከተል በመድረኩ ላይ ከታደሙ የተለያዩ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ሀሳቦች ተሰጥተው መድረኩ ፍፃሜውን አግኝቷል።