በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ሀገራችንን የሚወክሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ ቡና በሜዳቸው ጨዋታ ማድረግ እንደማይችሉ ታውቋል።
በየእርከኑ የሚደረጉ የሀገራችን የውስጥ ሊግ ውድድሮች እየተገባደዱ የሚገኝ ሲሆን በወንዶች ዘርፍ የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ እርከን ውድድር የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀገራችንን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እንዲሁም ዘንድሮ በአዲስ መልክ የተከናወነው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በኮንፌዴሬሽን ካፕ መሳተፋቸውን ካረጋገጡ በኋላ ከትናንት በስትያ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል።
በካፍ ፍቃድ ያለው ሜዳ ባለመኖሩ ብሔራዊ ቡድናችን በተለያዩ አጋጣሚዎች በገለልተኛ ሜዳ ሲጫወት መክረሙ አሁንም በክለቦቻችን ቀጥሎ ባንክ እና ቡና በደጋፊያቸው ፊት የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን መከወን እንደማይችሉ ይፋ ሆኗል። ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ የካፍ የክለቦች ውድድር የሚደረግባቸው የየሀገራቱ ስታዲየሞች ዝርዝር ላይ የሀገራችን ሜዳ አለመኖሩም ታውቋል። በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ቡና ተጋጣሚ ኬኒያ ፖሊስም በሜዳው መጫወት እንደማይችል ተመላክቷል።
ሁለቱ የሀገራችን ክለቦች የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን በየትኛው ሀገር ገለልተኛ ሜዳ እንደሚያደርጉ እየተከታተልን መረጃውን የምናቀርብ ይሆናል።