የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የሸገር ደርቢ ጨዋታ የአሜሪካ ጉዞ ከምን ደረሰ?

በያዘነው ሐምሌ ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም የሸገር ደርቢ ጨዋታ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉት ጉዞ በተመለከተ የተጠናከረ ዘገባ

የካቲት 22 ቀን በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደ ስነ ሥርዓት የአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር ተሳታፊ የሆነው ዲሲ ዩናይትድ ተወካዮች ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመው ነበር። በወቅቱ በመድረኩ እንደተጠቀሰው ከሆነ ከመሠረተ ልማት ጋር የተገናኙ ስራዎችን ለመስራት የታለመ ስምምነት ቢሆንም በያዝነው ሐምሌ ወርም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ አቅንቶ ከክለቡ ጋር የጉብኝት የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ በስምምነቱ ተጠቅሶ ነበር።

በዚህ ብቻ ያልተገደበው ስምምነቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ባደረጉት ስምምነት ሐምሌ 12 ወደ አሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ አምርተው የእርስ በእርስ የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርጉ እንደሆነ ቀጠሮ መያዙን በወቅቱ ተገልፆ ነበር።

ሶከር ኢትዮጵያም ይህ ከአራት ወር በፊት የተደረገው ስምምነት ከምን ደረሰ ስትል የጉዳዮ ባለቤት የሆኑትን ሁለቱን አካላት አናግራ ተከታዮን ምላሽ አግኝታለች።


በሸገር ደርቢ ጨዋታ ዙርያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ ሐምሌ 12 ሊደረግ የታሰበው ጉዞ የቀን ለውጥ እንደተረገበት አንስተው በቀጣይ መቼ ጉዞው እንደሚሆን አሁን ላይ እንዲህ ብሎ መናገር እንደማይቻል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አሰርፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው በብሔራዊ ቡድኑ ጉዞ ዙርያ በሰጡን ምላሽ“ የቀን ለውጥ ይኖራል።” ተደራራቢ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መኖሩ ለቀን ለውጥ መደረጉ ምክንያት እንደሆነ አውስተው በቀጣይ ጉዞው የሚደረግበትን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።