መቻል የአሰልጣኙን ውል ለማራዘም ተስማምቷል

ያለፉትን አስራ ሁለት ወራት መቻልን ውጤታማ ያደረጉት አሰልጣኝ በቡድኑ እንደሚቆዩ ተወስኗል።

80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ክንዋኔዎች በደማቅ ሁኔታ አክብሮ ያጠናቀቀው መቻል ስፖርት ክለብ ለቀጣይ የውድድር ዓመት በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ ለመቅረብ ከወዲሁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ መጀመሩን ሰምተናል።

በትናትነው ዕለትም የክለቡ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ የውል ዘመናቸው የተጠናቀቀውን የዋና አሰልጣኙ ገብረክርስቶስ ቢራራን ውል የማራዘም ስራዎችን ለመስራት ውይይት ካደረገ በኋላ አሰልጣኙ ለተጨማሪ ዓመት በክለቡ የሚቆዮበትን ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም መሰረት አሰልጣኝ ገብረ ክርስቶስ ቢራራ ከመቻል ጋር ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት የሚቆዩበት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን አብረዋቸው የሚሰሩትን ምክትል አሰልጣኝ በቀጣይ እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል።

ያለፈውን አንድ ዓመት ቡድኑን የተረከቡት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ መቻል ከባለፉት ተከታታይ ዓመታት ዝቅተኛ ውጤት ዘንድሮ በተሻለ ደረጃ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንዲቆይ አስችለውት በመጨረሻው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ በመሆኑ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።