ወላይታ ድቻ የተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር ቋጭቷል

አመሻሹን ወደ ዝውውሩ የገቡት ወላይታ ድቻዎች የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቁ የነባሮችን ውልም አድሰዋል።

አመሻሹን ወደ ዝውውሩ በመግባት አማካዩ ሙሉቀን አዲሱን ወደ ስብሰባቸው የቀላቀሉት ወላይታ ድቻዎች የሁለት ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ሲቀላቅሉ የሁለት ነባሮችን ውልም ማደሳቸው ታውቋል።

ቴዎድሮስ ታፈሰ አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ሆኗል። በመቻል ክለብ ውስጥ ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ እስከ ዋናው ድረስ ግልጋሎት በመስጠት ሰባት ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በመቀጠል በሲዳማ ቡና እንዲሁም የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ካሳለፈ በኋላ የሶዶውን ክለብ ተቀላቅሏል።

ተከላካዩ ውብሸት ክፍሌም አሰዳጊ ክለቡን ተቀላቅሏል። ከወላይታ ድቻ ተስፋ ቡድን መነሻውን ያደረገው ተጫዋቹ በጉዳት ከተፈተነ የእግር ኳስ ህይወቱ በኋላ በሶዶ ከተማ ፣ ቦዲቲ እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በአዲስ አበባ ቆይታ አድርጎ ወደ ልጅነት ክለቡ አምርቷል።

ወላይታ ድቻ ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የክለቡ ፍሬ የሆኑ እና ውላቸው ተጠናቆ የነበረውን የአማካዩ መሳይ ኒኮል እና የተከላካዩ አዛሪያስ አቤልን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት አራዝኗል።