ጦሩ ሁለት አጥቂዎችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

ከቀናት በፊት የአሠልጣኙን ውል ያደሰው መቻል ወደ ዝውውሩ በመግባት ሁለት ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መልካም የሚባል ጉዞ በማድረግ እስከ መጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ድረስ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የዘለቁት መቻሎች ከአምስት ቀናት በፊት የአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን ውል ካደሱ በኋላ ፊታቸውን ወደ ዝውውሩ በማዞር ስብስባቸውን ማጠናከር ጀምረዋል። ከደቂቃዎች በፊትም ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ጦሩን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች ዳንኤል ዳርጌ ነው። የቀድሞ የደቡብ ፖሊስ እና የገላን ተጫዋች የነበረው ዳንኤል ኦሮሚያ ፖሊስን ከተቀላቀለ ጀምሮ ምርጥ ብቃቱን በከፍተኛ ሊጉ ሲያሳይ የነበረ ሲሆን ከአህመድ ሁሴን ጋርም የከፍተኛ ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን በ18 ጎሎች ይዞ አጠናቋል። ተጫዋቹን በሁለት ዓመት ውል የመቻል ንብረት መሆኑ እርግጥ ሆኗል።

ሁለተኛው ተጫዋች ፊሊሞን ገብረፃዲቅ ነው። ከኢትዮጵያ ቡና የታዳጊ ቡድን የተገኘው ፊሊሞን ከሁለት ዓመታት በፊት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ የቡድኑ አባል ሲሆን ከዛም ወደ ኮልፌ ቀራኒዮ ካመራ በኋላ ዘንድሮ በጅማ አባጅፋር ግልጋሎት ሰጥቶ መቻልን እንደ ዳንኤል በሁለት ዓመት ውል ተቀላቅሏል።