ኢትዮጵያ ቡና የአሰልጣኙን ውል አራዘመ

ዓመቱን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ያሳለፈው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ለተጨማሪ ዓመት በቡናማዎቹ ቤት ይቆያል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ዓመቱን በፕሪምየር ሊጉ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ከማጠናቀቁ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ባሳካው የዋንጫ ድል መነሻነት በካፍ የክለቦች የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆኑ ይታወቃል። ቡድኑ ከቀናቶች በፊት ከከፍተኛ ሊጉ አዳዲስ ተጫዋቾንን ያስፈረመ ሲሆን አሁን ደግሞ ዘግየት ብሎ የአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬን ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝሟል።

በትውልድ ሀገሩ ነገሌ ቦረና ስልጠናን የጀመረው እና በመቀጠል በሲዳማ ቡና ታዳጊ ቡድን ፣ በወልቂጤ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እንዲሁም ደግሞ በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ያገለገለ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡናም የረዳት አሰልጣኝነት ሚናን በመጨረሻም ከሰርቪያዊው አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች ስንብት በኋላም የቡናማዎቹ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ ካገለገለ በኋላ ለቀጣዩ አንድ ዓመት ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት ለማገልገል በዛሬው ዕለት ቡድኑ ውሉን አራዝሞለታል።