የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ኦፒያን አናሊቲክስ አብረው ለመሥራት ተስማሙ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከኦፒያን አናሊቲክስ ተቋም ጋር በማማከር፣ በሲስተም ግንባታ እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምቷል።

ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተሰጠው መግለጫ የኦፒያን አናሊቲክስ ተወካይ የሆኑት አቶ ዘላለም ግዛቸው የቴክኖሎጂ ተቋማቸው ላለፉት 10 ዓመታት ተቋምን ለማሻሻል እና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እንዴት ተቋማት Data’ን እንዴት መጠቀም አለባቸው በሚል ሲሠሩ መቆየታቸውን አውስተው ከዚህ በፊት በጤና ሴክተሮች ላይ በስፋት መሥራታቸውን በመግለጽ አሁን ደግሞ በሌሎች ተቋማት ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው ዛሬ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የገቡት ስምምነት ለብዙ ነገሮች መነሻ እንደሆነ እና የኢትዮጵያ ዕድገት 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ወጣት ከመሆኑ አንጻር በቴክኖሎጂ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል እና ተቋማት በቴክኖሎጂ ካልታገዙ ከሌላው ዓለም ወደኋላ ሊቀሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል። አቶ ዘላለም አክለውም እንደ ድርጅት ባላቸው አቅም ተቋማትን ለመደገፍ ፅኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸው እግርኳስ ከመዝናኛነት ባሻገር ሀገር የመገንባት አቅም እንዳለው ተናግረው በተለይም የኢትዮጵያ እግርኳስ በቴክኖሎጂ ቢደገፍ ሀገር የመገንባት አቅም እንዳለው ሀሳባቸውን ሲሰጡ ፌዴሬሽኑ እግርኳሱን በስርዓት እንዲያስተዳድር እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እግርኳስ እንዲፈጠር ተቋሙ ሊደገፍ እንደሚገባ አሳስበው ይህም ከፌዴሬሽኑ ጋር አብረው ለመሥራት እንዳነሳሳቸው እንዲሁም የተጫዋቾችን ዳታ ከታች ጀምሮ በተደራጀ ሁኔታ ስትራቴጂካሊ ለማስቀመጥ እና ለማስተዳደር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ባሕሩ ጥላሁን በበኩላቸው ስምምነቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው በተለይም ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ እና መረጃዎችን ሰንዶ ይዞ በቀላሉ ተደራሽ በማድረጉ በኩል በፌዴሬሽኑ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማጥበብ የሚያስችል መፍትሔ እንደሆነ ጠቅሰው ፌዴሬሽኑ ያደጉ ሀገራት ያላቸውን የዳታ አያያዝ እንዲኖረው እንደሚፈልጉ በመግለጽ በሌሎች ሀገራት እንደ ሀገር ከጫፍ እስከ ጫፍ የተጫዋቾች ሙሉ መረጃ የተያዘ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ክለቦች ላይ ያሉ ተጫዋቾች መረጃ ብቻ ሊገኝ እንደሚችል ስለዚህም ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችል ፕላትፎርም ስላልነበረ ይህ ስምምነት ግን ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረው መረጃ ከአንዱ ዲፓርትመንት ወደ ሌላው ከማድረስ አንጻር እና በብሔራዊ ቡድን ዙሪያም የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የተጫዋቾቹን ሙሉ መረጃ ማግኘት የሚችሉበት የተሻለ ግንዛቤ እና መፍትሔ መውሰድ የሚቻልበት እንደሆነ ተናግረው እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስምምነቱን በደስታ መቀበላቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በቦታው ከተገኙ ጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቶ መርሐግብሩ ተጠናቋል።