ወልዋሎ ዓ/ዩ ጋናዊ አማካይ ለማስፈረም ተስማማ

አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን የሾመው ወልዋሎ ዓ/ዩ በዝውውር መስኮቱ የመጀመሪያ ተጫዋች ለማግኘት ከጫፍ ደርሷል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት በአስገዳጅ ሁኔታ ከውድድር ርቀው ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ በ2017 የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሳተፉን ካረጋገጠ በኋላ ስብስቡን ለማጠናከር ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። ባሳለፍነው ሳምንት አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን በመንበሩ ከሾመ በኋላም ፊቱን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር በማዞር በዛሬው ዕለት የመጀመሪያ ተጫዋች ለማስፈረም መስማማቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቢጫ ለባሾቹብ ለመቀላቀል የተስማማው ተጫዋች ጋናዊው ካዚም ራዛክ ነው። የተከላካይ አማካዩ ካዚም ራዛክ ረዘም ያለ ግልጋሎት ከሰጠበት አክራ ግሬት ኦሎምፒክስ ክለብ ጋር በውድድር ዓመቱ ከተለያየ በኋላ ሌላኛውን የሀገሩን ክለብ ኸርትስ ኦፍ ኦክ ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ከወልዋሎ ጋር የነበረው ድርድር ተጫዋቹ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዞር እንዳደረገው ተጠቁሟል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሀገሩን ያገለገለው ተጫዋቹም የአንድ ዓመት ውል ለመፈፀም ስምምነት ላይ ደርሷል።