መቻል ጠንከር ያሉ ዝውውሮችን መፈፀሙን ገፍቶበታል

ከደቂቃዎች በፊት አማኑኤል ዮሐንስን የግሉ ያደረገው መቻል አሁን ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምቷል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀው መቻል በዝውውር ገበያው በስፋት በመግባት የፊሊሞን ገብረፃዲቅ እና የዳንኤል ደርቤን እንዲሁም ከደቂቃዎች በፊት የአማኑኤል ዮሐንስን ዝውውር ማጠናቀቁ ይታወቃል። አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል።

የመጀመሪያው ተጫዋች አማካዩ አብዱልከሪም ወርቁ ነው። በኢትዮጵያ መድን የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው አብዱልከሪም በማስከተል በወልቂጤ ከተማ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በቡናማዎቹ ቤት ቆይታ ማድረጉ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ዋንጫን ከቡና ጋር ያነሳው ተጫዋቹ ቀጣይ የእግርኳስ ህይወቱን በመቻል ለማሳለፍ በዛሬው ዕለት ስምምነት ፈፅሟል።

በፋሲል ከነማ መለያ ብቻ የምናቀው ዓለም ብርሀን ይግዛው መቻልን የተቀላቀለው ተጫዋች ሲሆን ያለፉትን ዓመታት በቀኝ መስመር በፋሲል ከነማም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ጊዜ ማሳለፉ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ዋንጫን ከፋሲል ጋር ያነሳው ዓለም ብርሀን ከስድስት ዓመታት በላይ ከቆየበት ክለቡ ጋር በመለያየት ወደ መቻል ማምራቱ ታውቋል።

ሁለቱም ተጫዋቾች የሁለት ዓመት ውል ለመፈረም መስማማታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ መረጃ አግኝታለች።