“የኢትዮጵያ እግርኳስ እናስተካከል ከተባለ ምንም መደባበቅ ፤ መወሻሸት አያስፈልግም።” አቶ ባህሩ ጥላሁን

የወቅቱ መነጋገሪያ ርዕስ በሆነው አዲሱ የተጫዋቾች ዝውውር መመርያ ዙርያ እየተሰጠ ባለው ጋዜጣዊ መግለጫ የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከደሞዝ መግለፅ ጋር በተገናኘ ምን አሉ ?

በካፒታል ሆቴል አስቀድመን ባጋራናቹሁ መረጃ መሰረት የሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰፊ ማብራሪያ እና ከሚዲያ አካላት የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛል። ትኩረት የሚስቡትን ሀሳቦች ይዘን እንደምንቀርብ በገለፅነው መሰረት ፌዴሬሽኑ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ከትናትናው ጀምሮ የተጫዋቾችን ያልተጣራ ደሞዝን ይፋ ማድረግ መጀመሩ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ በቦታው ከሚገኙ የሚዲያ አካላት “የተጫዋቾችን ወርሐዊ ደሞዝ ያለ ተጫዋቹ ፍቃድ መጥቀሱ ምን ያህል አግባብ ነው?” ተብለው የተጠየቁት የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

“ የኢትዮጵያ እግርኳስ እናስተካከል ከተባለ ምንም መደባበቅ መወሻሸት አያስፈልግም። የስራ ማስታወቂያ ሲወጣ በይፋ የተቀጣሪው ደሞዝ ይገለፃል። ለምሳሌ በስምምነት አልያም በሌላ መንገድ የሚወጣበት አሰራር አለ። በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አሰልጣኝ ስንቀጥር ደሞዝ ተጠይቀን እናውቃለን። የተጫዋቾች ይፋ ሲሆን ይህን የተለየ ሚያደርገው ለምድነው? በአሁኑ ወቅት መንግስትም እያበረታታው ይገኛል። ከዚህ ቀደም ያስቀመጥነው አሰራር አለ። የተጫዋቾች አካውንት የማስቀመጥ። ስለዚህ በግልፅ ማስቀቀመጡ ከህግ አንፃር ክፍተቱ አልታየንም። የእኛም ትልቅ ተቋም ነው ፤ ዝም ብሎ የሚመራ አይደለም። የህግ ባለሙያ አማክረን ነው ያወጣነው። ፔሮል ኦፊሻል መረጃ ነው። የተጫዋችም ደሞዝ ይፋ መሆኑ ይቀጥላል። መንግስትም ተገቢውን ታክስ መሰብሰብ አለበት።”