ስለ ተጫዋቾች ዝውውር እና የክለቦች ክፍያ አስተዳደር መመሪያ አተገባበር መግለጫ ተሰጥቷል

“መሬት እንሰጣችኋለን ብለው ተጫዋች ለማስፈረም የሚጥሩ ክለቦች እንዳሉ ሰምተናል።” መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ

“እንደዚህ ደንብ የመመሪያ ማስጨበጫ የተሰጠበት ደንብ ዐይተን አናውቅም።” አቶ ክፍሌ ሰይፈ

“ክለቦች ካፍ የሚፈልገውን ፎርማሊቲ እንዲያሟሉ እናደርጋለን።” አቶ ባሕሩ ጥላሁን

ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በካፒታል ሆቴል በተሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ፤ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ባሕሩ ጥላሁን ተገኝተው የክፍያ ስርዓት መመሪያውን አተገባበር አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በቅድሚያ ንግግራቸውን የጀመሩት የቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ አክሲዮን ማኅበሩ የሠራቸውን ሥራዎች ለመጠቆም ያህል በተለይም አስቸጋሪ ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነውን የፋይናንስ አድሚንስቴሬሽን በተመለከተ ክለቦች ካሉበት ደረጃ በምን እናሻሽላቸው በማለት እንዲሁም ለዕድገታቸው ምቹ የሆኑ ስልጠናዎችን መስጠታቸውን ለአብነት ያህል ስለ ክለብ ማኔጅመንት ፤ አንድ ክለብ “ክለብ” የሚባለው ምን ሲያሟላ ነው? በሚለው ጉዳይ ከሆላንድ በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና እንደተሰጠ ከዛ አልፎም ስለ ብራንዲንግ እና ሎጎ ፣ ስለ ስፖንሰርሺፕ ሰፊ ስልጠና መሰጠቱን እንዲሁም ለአውሮፓ ክለቦች ስልጠና በሚሰጡ የሆላንድ አሰልጣኞች ለአሰልጣኞች ሦስት ጊዜ ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመው ለዳኞች ሁለት ጊዜ ከውጪ በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና እንደተሰጠም ሀሳባቸውን ገልጸው በሕግ አተገባበሩ ላይ ያላቸውን አቋም “ወይ ሕጉ ይተገበራል ፣ ወይ ሊጉ ይፈርሳል” ሲሉ አበክረው አስታውቀዋል።


በመቀጠል ሀሳባቸውን የሰጡት የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በበኩላቸው መመሪያው ብዙ እንደተለፋበት እና ከወጣ በኋላም 16ቱ ቡድኖች እንደፈረሙበት አስታውቀው የክፍያ ስርዓቱ ቼክ እና ቅድመ ክፍያ እንደሚከለክል እሱም ተግባራዊ ተደርጎ ተጫዋቾች እየፈረሙ እንደሚገኙ ጠቁመው ቡድን መሥራት የማይችሉ የተወሰኑ የስፖርቱ አካላት “የጥቂት ሰዎች ፍላጎት ነው” ሲሉ እየወቀሷቸው እንደሚገኙ ገልጸው ከዚህ በፊት የደመወዝ ጣሪያ 50ሺህ ብር የተወሰነ ጊዜ በከፍተኛ ፍላጎት መመሪያውን ያጸደቁ ክለቦች ማታውን እንዳፈረሱት አውስተው እንዲህ ዓይነት መግለጫ ከተሰጠ በኋላ በጋዜጠኞችም ሆነ በስፖርት ቤተሰቡ የሚሰጡ ግብረመልሶች አነስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በበኩላቸው ክለቦች ተጫዋች ለማስፈረም ሲመጡ የተጫዋቾቹ የአደጋ ጊዜ እና የሕይወት መድኅን ሽፋን እንዲሁም የተጫዋቹ የጤና ምርመራ ውጤት እንደሚያስፈልግ አበክረው በመግለጽ የዕድሜ ማጭበርበሮች እንዲቀንሱ የልደት ሰርተፊኬት ለመያዝ ማቀዳቸውን አሳስበዋል።

በመቀጠል በስፍራው ከተገኙ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው መልስ ተሰጥቶባቸዋል።

ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት ቀዳሚ የነበሩት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የክለብ አመራሮች ለመረጃ ክፍት ስላለመሆናቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ አብዛኞቹ ክለቦች አሠራራቸው ትክክል ስላልሆነ ለጋዜጠኞች መግለጫ ለመስጠት እንደሚፈሩ ሆኖም ግን ትላልቅ የሚባሉ ክለቦች በአንጻራዊነት ለሚዲያ ክፍት መሆናቸውን ሲጠቁሙ ሊግ ካምፓኒው በጭምጭምታ ሰማኋቸው ስላላቸው ነገሮች ሲጠየቁም “በጭምጭምታ የሰማነው ፈርሙ እና መሬት ይሰጣችኋል የሚል ሲሆን ደረቅ ቼክ መስጠት ፣ በእናትም በአባትም ስም ቢሆን ለመስጠት እንደታሰበ ፣ ከነጋዴው በሚሰበሰብ ገንዘብ በሌላ መንገድ ለመክፈል ቢታሰብም ሁሉም እንደማይቻል አሳስበው ሁሉም የቡድን አባላት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት እንደሚከፍቱ እና የመበርበር መብት እንዲኖራቸውም ሁሉም በፊርማ ማረጋገጡን ተናግረው ቅሬታ ያላቸው አሉ የተባሉ አካላትም ሁሉም “አደራ ወደኋላ እንዳትሉ ትልቅ እርምጃ ይወሰድ መብት ለሚጥሱት” ብሎ ነው ሁሉም የወጣው ብለው ደመወዝ ላይ ሳይሆን ዋናው ጉዳያቸው የፋይናንስ አስተዳደሩን ማስተካከል እንደሆነ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል ።

የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ “እንደዚህ ደንብ የመመሪያ ማስጨበጫ የተሰጠበት ደንብ ዐይተን አናውቅም” ካሉ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ክለቦች መሠረታዊ የአደረጃጀት ችግር እንዳለባቸው እና ለሙያው በሚጨነቁ ሰዎች እየተመራ እንዳልሆነ ጠቁመው ለምሳሌ ያህል በመመሪያው ላይ ቅሬታ ካቀረቡ አሰልጣኞች መካከል የአንዱ ቡድን ለአራት ዓመታት ደመወዝ ባለመክፈሉ ፍርድ ቤት እየተመላለሰ እንደሆነ ገልጸው አብዛኞቹ ክለቦች በከተማቸው በሚገኝ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እንደሚጠቀሙ ይባስ ብሎም ወንበር እንኳ ሳይቀይሩ በመቶ ሚሊዮኖች ማውጣታቸው አሳፋሪ አሠራር ነው ሲሉ ኮንነው ዛሬ ላይ የቅድመ ክፍያ የሚፈጽሙ አብዛኞቹ ክለቦች መስከረም ወር ላይ ደመወዝ እንደማይሰጡ ተናግረዋል።


በመጨረሻም ሀሳብ የሰጡት የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን የተጫዋቾች ደመወዝ ይፋ ስለመደረጉ የኢትዮጵያን እግርኳስ እናስተካክል ካልን ብዙ የጀመርነው ነገር አለ ካሉ በኋላ “የብሔራዊ ቡድን ኮቺንግ ስታፍ ስንቀጥር ደመወዝ እንጠየቃለን። ለተጫዋቾች ሲሆን ለምን አዲስ ይሆናል? ብለው መንግሥትም ይህንን ጉዳይ እንደሚያበረታታው እና ኦፊሺያሊ ማሳወቁ ከሕግም አንጻር ተጠያቂ ያደርጋል ወይ ለሚለው የሕግ አማካሪዎችን አማክረን ነው በግምት አላደረግንም ብለው መንግሥትም በአግባቡ ታክስ መሰብሰብ ስላለበት ነው በማለት ደላላ ጋዜጠኞች ስለተባለው “ሕጋዊ ሆኖ የተመዘገበ ኤጀንት ጋዜጠኛ የለም በሩቅ ስለሚሰሙ ነገሮች ጥልቅ ጥናት ይፈልጋል።” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም ለምሳሌ ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች እንዳስፈረመ በክለቡ ፔጅ ይፋ ተደርጎ በፌዴሬሽኑ ግን ይፋ ስላለመደረጉ ተጠይቀው ንግድ ባንክ እና ቡና በኢንተርናሽናል ውድድሮቻቸው ምክንያት ስፔሻሊ ተፈቅዶላቸው ነው ያስፈረሙት ኦፊሻል ለማድረግ ግን የሚቀሩ ዶክመንቶች ስላሉ ነው። ካሉ በኋላ በርካታ ክለቦች በCLOP ፎርም እንዲሞሉ ለምሳሌ የሴት ክለብ ሳይኖራቸው አለን በሚል በስህተት ፎርም የሞሉ አሉ ውሳኔ ይሰጥባቸዋል ብለው በስተመጨረሻም “ካፍ የሚፈልገውን ፎርማሊቲ እንዲያሟሉ እናደርጋለን ፤ ከስያሜ ጋር ተያይዞም መቅደም ያለበት ይቅደም ተብሎ እንጂ ከአርማ ጀምሮ ይህንን ስንጨርስ ወደ ማስተካከሉ እንሄዳለን።” የሚል ወሳኝ መልዕክት አስተላልፈዋል።