ድሬደዋ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ አግኝቷል

በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቁት ብርቱካናማዎቹን አዲስ አሰልጣኝ አግኝተዋል።

በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን በሁለት አሰልጣኞች እየመራ ነበር ዓመቱን የቋጨው የምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ። በአሰልጣኝ አስራት አባተ መሪነት የሊጉን አካፋይ ዓመት ሲመራ ከሰነበተ በኋላ ረዳት አሰልጣኝ የነበረውን ኮማንደር ሽመልስ አበበን በጊዜያዊ መንበሩ በመሾም የውድድር ዓመቱን መፈፀም የቻሉት ብርቱካናማዎቹ ለቀጣዩ የ2017 የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር ያሳለፈውን አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን በመንበሩ ሾመዋል።

ከአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን የስልጠና ህይወቱን የጀመረው እና በመቀጠልም በዛው የዕንስት ቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ካገለገለ በኋላ በፋሲል ከነማ ፣ ሰበታ ከተማ እና አዳማ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ካገለገለ በኋላ በ2014 አጋማሽ ላይ አዳማን በዋና አሰልጣኝነት ተረክቦ እስከ ተጠናቀቀው ዓመት ድረስ በቡድኑ ውስጥ ቆይታ ነበረው። አሠልጣኙም አዲስ አበባ ወይም ድሬዳዋ በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ቡድኑን በይፋ እንደሚረከብ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል