መቻል የሦስት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው መቻል በዛሬው ዕለት የሦስት ነባር ተጫዋቾቹን ውል ለተጨማሪ ዓመታት አራዝሟል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መልካም የሚባል ጊዜ በማሳለፍ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው መቻል በቀጣዩ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ የአሠልጣኙን ውል ካራዘመ በኋላ ወደ ዝውውሩ በመግባት አማኑኤል ዮሐንስ፣ አብዱልከሪም ወርቁ፣ ዓለምብርሃን ይግዛው፣ ዳንኤል ዳርጌ እና ፊሊሞን ገብረፃዲቅን የግሉ ማድረጉን ዘገባ አቅርበን ነበር። አሁን ደግሞ የነባር ተጫዋቾቹን ውል ማደስ ጀምሮ የሦስት ተጫዋቾችን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ውሉን ያደሰው የመጀመሪያው ተጫዋች አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ነው። ዘንድሮ ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ የነበረው ምንይሉ ለቡድኑ 15 ግቦችን በተጠናቀው የውድድር ዓመት ማስቆጠሩ አይዘነጋም።

ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ የመስመር ተከላካዩ ዳዊት ማሞ ነው። ለስድስት ዓመታት በቡድኑ ግልጋሎት የሰጠው ታታሪው ተከላካይ ሁለተኛ ውሉን ያደሰ ጦረኛ ነው።

ሦስተኛው ተጫዋች ደግሞ የመሐል ተከላካዩ ነስረዲን ኃይሉ ነው። የቀድሞ የለገጣፎ እና ገላን ተጫዋች የነበረው ነስረዲን ዓምና መቻልን ከተቀላቀለ በኋላ በተለይ በሁለተኛ ዙር ጥሩ ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን ውሉንም በክለቡ አራዝሟል።