መቻል የሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

ስብስቡን እያጠናከረ የሚገኘው መቻል ከደቂቃዎች በፊት የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ውል አድሷል።

በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው መቻል ያለፉትን ሁለት ቀናት አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የነባር ተጫዋቾችን ውል ማደስ ይዟል። ከሰዓታት በፊትም የምንይሉ ወንድሙ፣ የነስረዲን ኃይሉ እና የዳዊት ማሞን ውል ያደሰው ክለቡ አሁን ደግሞ የተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ውል ለተጨማሪ ዓመታት አራዝሟል።

ውሉን ታደሰው የመጀመሪያው ተጫዋች በረከት ደስታ ነው። ከአዳማ ወጣት ቡድን የተገኘው በረከት ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ እስከ 2012 ቆይታን አድርጎ ወደ ፋሲል ከነማ አምርቶ መጫወቱ አይዘነጋም። 2014 ክረምት ላይ ወደ መቻል ቤት አምርቶ ያለፉትን ሁለት ዓመታት የተጫወተው በረከት በዛሬው ዕለት በጦሩ ቤት ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት ተስማምቷል።

ሁለተኛው ውሉን ያደሰው ተጫዋች ደሳለኝ ከተማ ነው። የቀድሞ የደብረብርሃን እና አውስኮድ ተጫዋች የነበረው ተከላካዩ እንደ በረከት ሁለት ዓመት ከቆየበት መቻል ጋር ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ለማገልገል ተስማምቷል።