ኢትዮጵያ ቡና ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክለው ኢትዮጵያ ቡና በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የሚጀምርበትን ቀን ዝግጅት ክፍላችን ማወቅ ችላለች።


የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ በመሆኑ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክለው ኢትዮጵያ ቡና በቅድመ ማጣሪያ መርሐግብር ከኬኒያ ፓሊስ እንዲሁም በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ከንግድ ባንክ እና በ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለሚኖሩ ውድድሮች የቅደመ ውድድር ዝግጅቱን መቼ እና የት እንደሚጀምር ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከከፍተኛ ሊጉ ኦካይ ጁል ፣ እስራኤል ሸጎሌ እና ዳዊት ሽፈራውን ከሀገር ውጪ ደግሞ ጋናዊውን ግብ ጠባቂ ኢብራሂም ዳንላድ የብሩንዲ ዜግነት ያለውን የመስመር አጥቂ አልፍሬድ ኑኩሪንዚዛ ወደ ስብስባቸው ከቀላቀሉ በኋላ በመጨረሻም በትላንትናው ዕለት ደግሞ ጊዜያዊ አሰልጣኙ ነጻነት ክብሬን በዋና አሰልጣኝነት ውሉ ተራዝሞለታል። ቡድኑ የፊታችን እሁድ ሐምሌ 21 የቡድኑን አባላት በመያዝ ወደ አዳማ ከተማ በማምራት ማረፊያውን በአቤል ገስት ሀውስ አድርጎ በማግስቱ ዕለተ ሰኞ ሐምሌ 22 በይፋ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የሚጀምር ይሆናል።