ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ተሳታፊ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ በተደጋጋሚ የሊጉን ክብር በማሳካት የሚታወቀው እና ዘንድሮም በሊጉ የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ለአራተኛ ጊዜ ይወክላል። ቡድኑ ሀገራችን አዲስ አበባ ላይ ለሚደረገው የዞኑ የማጣሪያ ጨዋታ ራሱን ለማጠናከር አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።


ቅድስት ዘለቀ የንግድ ባንክ አዲሷ ፈራሚ ሆናለች። እግር ኳስን በሀዋሳ ከተማ መለያ ሰባት ለሚጠጉ ዓመታት በመጫወት የቆየችው የመሐል ተከላካይዋ የእግር ኳስ ሁለተኛ ክለቧ አድርጋ የአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን ቡድን ተቀላቅላለች። ሌላኛዋ ፈራሚ አጥቂዋ ሳራ ነብሶ በአዳማ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮ ኤሌትሪክ ተጫውታ ቀጣዩ ማረፊያዋ ንግድ ባንክ ሆኗል።

ንግሥት በቀለም ሦስተኛዋ ፈራሚ ሆናለች ከኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ከተገኘች በኋላ በመቀጠል በቦሌ ክፍለ ከተማ ያለፈውን ዓመት ደግሞ በመቻል የነበረችው ፈጣኗ አጥቂ ማረፊያዋ ንግድ ባንክ መሆኑ ዕርግጥ ሆኗል።

ተከላካዩዋ ታሪኳ ዴቢሶም በድጋሚ ወደ ቀደመ ክለቧ ተመልሳለች። ከሲዳማ ቡና የጀመረው የእግር ኳስ ሕይወቷ በቀጣይም በንግድ ባንክ ተጫውታ የነበረ ሲሆን ክለቡን በመልቀቅ ከመቻል ጋር ሁለት ዓመታትን ተጫውታ ዳግም ወደ ቀድሞው ቡድኗ የመለሳትን ዝውውር ቋጭታለች። አጥቂዋ መሠረት ወርቅነህም ከአርባምንጭ ከተማ እና መቻል በኋላ መዳረሻዋ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሆኗል።