የናይጀሪያ ሊግ የወቅቱ የወርቅ ጓንት ተሸላሚው ማረፊያ የኢትዮጵያ ክለብ ሆኗል

በ23/24 የናይጀሪያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ሆኖ የጨረሰውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም የሀገራችን ክለብ ተስማምቷል።

ፋሲል ከነማ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሰፊ የዋንጫ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች አንዱ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የታሰበው ሳይሆን ሊጉን ስድስተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

በቀጣይ ዓመት ራሳቸውን አጠናክረው ለመቅረብ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት እየተጉ የሚገኙት ዐፄዎቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ውሉን ያጠናቀቀውን በረከት ግዛውን ለማስፈረም ከተስማሙ በኋላ ባለፈው የውድድር ዓመት የናይጀርያ ሊግ ወርቅ ጓንት አሸናፊው ኦማስ ኦባሶጊን ለማስፈረም መስማማታቸውን ሰምተናል።

በውድድር ዓመቱ በአስራ ስምንት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት በናይጀርያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን በበርካታ ጨዋታዎች ግቡን ያላስደፈረው ግብ ጠባቂው በቤንደል ኢንሹራንስ ያለውን ቆይታ በቅርቡ እንደሚወስን ካሳወቀ በኋላ ከሪቨርስ ዩናይትድ እና ኢኒምባ ጋር ስሙ ሲያያዝ ቢቆይም ማረፍያው የዐፄዎቹ ቤት ሆኗል። ግብጠባቂው በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ናይጀሪያ በነበረበት ጨዋታ ለብሔራዊ ቡድን ከተጠሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር።

በቀጣይ ቀናትም ወደ ሀገር ቤት በመምጣት በዐፄዎቹ ቤት ፊርማውን እንደሚያኖር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ላለፉት ሰባት ዓመታት የክለቡ ግብ ጠባቂ ሆኖ ያገለገለው ሚኬል ሳማኬ ቆይታም ያበቃለት ይመስላል።