ስሑል ሽረ ጋናዊ የመሀል ተከላካይ ለማስፈረም ተስማምቷል።
ቀደም ብለው አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ዋና አሰልጣኝ አድርገው የቀጠሩት ስሑል ሽረዎች ባለፈው የውድድር ዓመት ከሌጎን ሲቲ ጋር ያሳለፈውን ሱሌማን መሀመድ ለማስፈረም ተስማሙ። የ27 ዓመቱ የመሀል ተከላካይ ባለፈው የውድድር ዓመት በጋና ሻምፒዮንሺፕ 28 ጨዋታዎችን ማድረግ የቻለ ሲሆን ከቡድኑ ጋር ያለውን ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ማረፍያው ስሑል ሽረ ለመሆን ተቃርቧል። ሌጎን ሲቲን በአምበልነት የመራው ሱሌይማን በውድድር ዓመቱ በሁለት ጨዋታዎች የጨዋታውን ኮከብ ማሸነፍ ችሏል።
ከስሑል ሽረ በአንድ ዓመት ኮንትራት የተስማማው ይህ ተከላካይ በዝውውር መስኮቱ ኢትዮጵያ ቡና ከተቀላቀለው ኢብራሂም ዳንላድ፤ መቐለ 70 እንደርታ ለመፈረም ከተስማማው ሸሪፍ መሀመድ እና ወደ ወልዋሎ ካመራው ቃሲም ራዛቅ በመቀጠል ወደ አትዮጵያ ክለቦች የፈረመ አራተኛ ጋናዊ ለመሆን ከጫፍ ደርሷል።