ያሬድ ከበደ ወደ ቀድሞ ክለቡ ለመመለስ ተስማማ

መቐለ 70 እንደርታ የቀድሞ ተጫዋቹን ለማስፈረም ተስማማ።

በትናንትናው ዕለት ጋናዊው ተከላካይ ሸሪፍ መሐመድን ያስፈረሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ የቀድሞ ተጫዋቻቸው ያሬድ ከበደ ለማስፈረም ተስማምተዋል። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከመቻል ጋር ቆይታ የነበረው አማካዩ ከጦሩ ጋር የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሶ ለመጫወት ተስማምቷል። በውድድር ዓመቱ በስድስት ጨዋታዎች (89 ደቂቃዎች) ቡድኑን ያገለገለው ይህ ተጫዋች ምዓም አናብስት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድጉም ሆነ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሱ የጎላ ድርሻ ከነበራቸው ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ እንደነበር ሲታወስ አሁን ደግሞ በቂ የመሰለፍ ዕድል ያላገኘበትን መቻል ለቆ መቐለን ተቀላቅሏል።

ከዚህ ቀደም በአክሱም ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ሲዳማ ቡና እና መቻል የተጫወተው አማካዩ የቡድኑ የክረምቱ ሁለተኛ ፈራሚ ለመሆን ሲቃረብ በቀጣይ ቀናት በይፋ ፊርማውን ያኖራል ተብሎም ይጠበቃል።