ወልዋሎ አንድ ተጫዋች ሲያስፈርም ምክትል አሰልጣኝ ለመቅጠር ተቃርቧል

ቀደም ብሎ ወላይታ ድቻን ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ተጫዋች ወደ ቢጫዎቹ አምርቷል።

ከዓመታት በኋላ በተመለሱበት ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ወልዋሎዎች ቀደም ብሎ ወላይታ ድቻን ለመቀላቀል ተስማምቶ ማልያ ይዞ ፎቶ ተነስቶ የነበረውን ሠለሞን ጌታቸው አስፈርመዋል። በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ በነበሩት ሶዶ ከተማ ፣ ሀምበርቾ ፣ ጋሞ ጨንቻ ፣ ወልድያ እና ያለፈውን ዓመት ደግሞ በነቀምት ከተማ ቆይታ የነበረው ተጫዋቹ የቢጫዎቹ ሁለተኛ ፈራሚ ሆኗል።

ከወልዋሎ ጋር በተያያዘ ዜና ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ለመቅጠር መቃረቡ ለማወቅ ተችሏል፤ የአሸናፊ በቀለ ምክትል ሆኖ ለመስራት የተስማማው ደግሞ ከዚ ቀደም በወልዋሎ ታዳጊ እና ዋናው ቡድን ጨምሮ ሶሎዳ ዓድዋን በዋና አሰልጣኝነት ሲመራ የቆየው አታክልቲ በርኸ ነው።

የክለቡ ቦርድ ላለፉት ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ ሶሎዳ ዓድዋ ውጤታማ ቆይታ የነበረውን አሰልጣኝ በምክትልነት ለመቅጠር እንደወሰነ እና ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እንዳለ ሲታወቅ ላለፈው አንድ ዓመት ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የመራውና ላለፉት ዓመታት በምክትልነት ካገለገለው ሀፍቶም ኪሮስ ጋር በጋራ በምክትልነት እንደሚሰራም ታውቋል።