የባንክ ተጋጣሚ ከአሠልጣኙ ጋር ተለያይቷል

በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሀገራችንን ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚገጥመው ቪላ ከአሠልጣኙ ጋር ተለያይቷል።

የአህጉራችን የውስጥ ሊግ ውድድሮች ከተጠናቀቁ በኋላ አሸናፊዎች እና እንደየኮታው ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች የሚሳተፉበት የቻምፒየንስ ሊግ እና የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር የቅድመ ማጣሪያ ፍልሚያዎችን ከቀጣዩ ወር ጀምሮ መከናወን ይጀምራሉ። የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅድመ ማጣሪያው ከዩጋንዳው ሻምፒዮን ቪላ ጋር የተደለደለ ሲሆን ተጋጣሚውም በዛሬው ዕለት ቡድኑን አሸናፊ ካደረጉት ዋና አሠልጣኝ ጋር መለያየቱ ታውቋል።

ከ20 ዓመታት በኋላ የክለቡን የሊግ ዋንጫ ረሀብ ያስታገሱት የ42 ዓመቱ ሰርቢያዊ አሠልጣኝ ዱሳን ሱቱዋኖቪች ለአንድ ዓመት በቪላ ቤት አገልግለው ለክለቡ ዋንጫ ካመጡና የሊጉ ምርጥ አሠልጣኝ ክብርን ካገኙ በኋላ በቀጣይ ዓመትም ይቀጥላሉ ተብሎ ቢጠበቅም በስምምነት መለያየታቸው ይፋ ሆኗል። የመለያየታቸው ምክንያት በቅጡ ባይታወቅም ከዩጋንዳ እየወጡ ባሉ መረጃዎች የቡድኑን አምበል ጨምሮ ሌሎች ወሳኝ ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ክለቦች ማምራታቸው አሠልጣኙን አላስደሰተም።

ክለቡ በይፋ ባስታወቀው መረጃ መሠረትም የሱቱዋኖቪች ምክትል በመሆን ዓመቱን ያገለገለው ሞርሊ ቤክዋሶ በቀጣይ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ሆነው እንዲያገለግሉ ተሹመዋል።