አሸናፊ ሀፍቱ ከእናት ክለቡ ጋር ይቆያል

መቐለ 70 እንደርታ የመስመር ተጫዋቹን ውል ለማራዘም ተስማማ።


መቐለ 70 እንደርታ የመስመር ተጫዋቹ አሸናፊ ሀፍቱን ለተጨማሪ ዓመታት በክለቡ ለማቆየት እንደተስማማ ይፋ አድርጓል። ከመቐለ ሁለተኛ ቡድን ተገኝቶ ላለፉት ዓመታት ቡድኑን በማገልገል ላይ የቆየው ተጫዋቹ በከፍተኛ ሊጉ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከነበረው የስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ቡድኑ ተመልሶ ባለፈው የውድድር ዓመት የክልሉ ፌደሬሽን ባዘጋጀው ክልል አቀፍ ሊግ ሲሳተፍ ነበር ፤ ቡድኑ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳም ትልቅ ድርሻ ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል። አሁን ደግሞ ለተጨማሪ ዓመታት በክለቡ ለመቆየት ውሉን ያደሰ የመጀመርያው ተጫዋች ሆኗል።

ቀደም ብለው ጋናዊ ሸሪፍ መሐመድን ጨምሮ ሦስት የቀድሞ ተጫዋቾቻቸውን ለማስፈረም የተስማሙት መቐለዎች ባለፈው ዓመት ቡድኑን ያገለገሉ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ውል ለማራዘም በንግግር ላይ መሆናቸውም ታውቋል።