በረከት አማረ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ለመመለስ ተስማማ

ወልዋሎዎች የቀድሞ ግብ ጠባቅያቸው ለማስፈረም ተስማምተዋል።

ያለፉት አራት የውድድር ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ቆይታ የነበረው በረከት አማረ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ወልዋሎ ለመመለስ ከስምምነት ደርሷል። የተሻለ የመሰለፍ ዕድል ባገኘበትና ቡድኑን በአምበልነት በመራበት የውድድር ዓመት በ28 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ በ2413 ደቂቃዎች ቡድኑን ያገለገለው ግብ ጠባቂው ከሰይድ ሀብታሙና ፔፔ ሰይዶ በመቀጠል ከአስራ አምስት ጨዋታዎች በላይ አድርጎ ጥቂት ግቦች ያስተናገደ የሊጉ ሦስተኛ ግብ ጠባቂ ነው። አሁን ደግሞ ቀናት ከፈጀ ረዥም ድርድር በኋላ የአራት ዓመት የኢትዮጵያ ቡና ቆይታውን ቋጭቶ ወደ እናት ክለቡ ለመመለስ ከስምምነት ደርሷል።


የእግርኳስ ሕይወቱን በወልዋሎ ጀምሮ በሑመራ፣ አውሥኮድ፣ ፋሲል ከነማ፣ ወልዋሎ፣ ኢትዮጵያ ቡናና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ይህ ግብ ጠባቂ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ተመልሶ በቆየባቸው ዓመታትም የተሳኩ ጊዜያት አሳልፎ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ሲታወስ ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ ቢጫውን መለያ ዳግም ለብሶ ለመጫወት ተስማምቷል።