አህመድ ሁሴን ከአርባምንጭ ጋር ለመቆየት ተስማማ

ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱት አዞዎቹ የወሳኝ አጥቂያቸውን ውል አራዝመዋል።


በ2016 ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 18 ጎሎችን ከመረብ በማሳረፍ ከኦሮሚያ ፖሊሱ ዳንኤል ዳርጌ ጋር በጥምረት የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው አህመድ ሁሴን ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የሚቆይበትን ውል ለመፈረም መስማማቱን ክለቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አሳውቋል። በክልል ክለቦች ለአሰላ ከተጫወተ በኋላ በከፍተኛ ሊግ እና በፕሪሚየር ሊግ ለወልቂጤ የተጫወተው አህመድ ሁሴን ላለፉት ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜያት ካሳለፈበት አርባምንጭ ከተማ ጋር ውሉን ያራዘመ ተጫዋች ሆኗል።

በአሰልጣኝ በረከት ደሙ እየተመራ ከአንድ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሰው አርባምንጭ ከተማ የሌሎች ነባር ተጫዋቾችን ውል ለማደስም በንግግር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።