ዩጋንዳዊው አጥቂ ስሑል ሽረ ተቀላቀለ

ዩጋንዳዊው የፊት መስመር ተጫዋች የስሑል ሽረ ሁለተኛ ፈራሚ ሆኗል።

ቀደም ብለው ጋናዊው የመሀል ተከላካይ መሐመድ ሱሌይማን ለማስፈረም የተስማሙት ስሑል ሽረዎች አሁን ደግሞ ዩጋንዳዊው አጥቂ አሌክስ ኪታታ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

ከዩጋንዳው ቡል የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ስሑል ሽረ ለማቅናት ከስምምነት የደረሰው ይህ የ32 ዓመት አጥቂ ሴንት ሙኩኖ ከተባለው የመጀመርያ ክለቡ በኋላ ለ UPDF ፣ ቪላ ፣ ኪታራ፣ ጋዳፊ፣ ቡል እና ለሩዋንዳው ኪዮቩ ስፖርት መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሰው ለመወዳደር በዝግጅት ላይ ለሚገኙት ስሑል ሽረዎች ለመቀላቀል ተስማምቷል።


“ቤንዜማ” በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀውና ባለፈው የውድድር ዓመት ቡድኑ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ የረዱ አስር ግቦች ማስቆጠር የቻለው ይህ ዩጋንዳዊ አጥቂ ከጋናዊው መሐመድ ሱሌይማን ቀጥሎ ስሑል ሽረን ለመቀላቀል የተስማማ ተጫዋች ሆኗል።