አርባምንጭ ከተማ ሁለተኛ ፈራሚውን ለማግኘት ተስማምቷል

በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ቆይታ የነበረው አጥቂ ማረፊያው አዞዎቹ ቤት ሆኗል።

በሊጉ ላይ የነቃ ተፎካካሪ ለመሆን በርከት ያሉ የነባር ተጫዋቾችን ውል ሲያድስ የነበረው የአሰልጣኝ በረከት ደሙው ክለብ አርባምንጭ ከተማ ከደቂቃዎች በፊት የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ይሁን እንዳሻውን አዲሱ ፈራሚ ያደረገ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለተኛው አዲስ ተጫዋች በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ዓመቱን ያሳለፈው አጥቂ ሙሉጌታ ካሳሁን መሆኑን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጧል።

ከትውልድ ሀገሩ አዊ ቲሊሊ የእግር ኳስ ጅማሮውን ያደረገው ቁመታሙ አጥቂ በመቀጠል በእንጂባራ ከተማ ፣ አማራ ፓሊስ እና ዳሞት ከተማ በተባሉ የአማራ ክልል ክለቦች ውስጥ በክልል የሊግ ፣ የክልል ክለቦች እና በአንደኛ ሊግ ደረጃ የተጫወተ ሲሆን የተጠናቀቀውን ደግሞ በከፍተኛ ሊጉ ደሴ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን በቡድኑ ቆይታውም ጥሩ የውድድር ጊዜን በማሳለፉ በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ከአርባምንጭ ጋር ደሴ መደልደሉን ተከትሎ አሰልጣኝ በረከት ሲከታተሉት የቆዩ ሲሆን ለቀጣዩ ዓመት ደግሞ የቡድናቸው አዲስ ፈራሚ ከደቂቃዎች በፊት አድርገውታል።