ሲዳማ ቡና የኋላ ደጀን የግሉ ለማድረግ ተስማምቷል

ጠንከር ያሉ ዝውውሮችን እየፈፀመ የሚገኘው ሲዳማ ቡና የሊጉን ጠንካራ ተከላካይ ለማስፈረም ተቃርቧል።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ለቀጣይ የውድድር ዘመን ጠንካራ ቡድን ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ ሲገኝ አሁን ደግሞ የኋላ መስመራቸው ለማጠናከር ያለፉትን ስድስት ተከታታይ ዓመታት በወጥ አቋም ምርጥ ተከላካይነቱን ያሳየውን ያሬድ ባዬ የግላቸው ለማድረግ መስማማታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከአውስኮድ በቀጠል ለዳሽን መጫወት የቻለው ያሬድ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ ካነሳበት ዐፄዎቹ ቤት ስኬታማ ቆይታ ካደረገ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከጣና ሞገዶቹ ጋር የነበረውን ውል በዚህ ዓመት አጠናቋል። የተለያዮ ክለቦች እርሱን ለማስፈረም ጥያቄ ቢያቀርቡም የተጫዋቹ ማረፊያ ሲዳማ ቡና ሊሆን እንደሚችል ታውቋል።

ከሲዳማ ክለብ ኃላፊዎች ጋር ድርድር የተቀመጠው ያሬድ በአብዛኛው ነገሮች ከስምምነት መድረሱን እና የህክምና ምርመራ ማድረጉ የተሰማ ሲሆን ያላለቁ ነገሮች ሲጠናቀቁ በጥቂት ቀናት ውስጥ ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል።