የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ክለብ ሀዋሳ ከተማ የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር ቋጭቷል።
በቀጣዩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት ዘግየት ቢሉም ወደ ዝውውሩ በመግባት ቢኒያም በላይን ቀዳሚ ፈራሚ ያደረጉት በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች የቀድሞው ሁለት የታዳጊ ቡድን ውጤት የሆኑ ተጫዋቾችን በይፋ ስለማስፈረማቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የመሐል ተከላካዩ ወንድማገኝ ማዕረግ ሁለተኛው ፈራሚ ተጫዋች ሆኗል። በሀዋሳ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ የልጅነት የእግር ኳስ ጅምሩን ያደረገው እና ከ2008 እስከ 2013 ድረስ ከተጫወተ በኋላ ወደ ኢትዮ ኤሌትሪክ በማምራት ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በወልቂጤ ከተማ በማሳለፍ ቀጣዩ መዳረሻው የልጅነት ክለቡ ሀዋሳ መሆኑ ዕርግጥ ሆኗል።
ወንድማገኝ ኃይሉ ዳግም ወደ ሊጉ ተመልሷል። ወጣቱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ልክ እንደ ወንድማገኝ ማዕረግ ሁሉ የሀዋሳን የወጣት ቡድኖች ካገለገለ በኋላ በ2012 ወደ ሀዋሳ ዋናው ቡድን አድጎ የተጫወተ ሲሆን በዓመቱም የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋችን ክብርን ማሳካቱ ለብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት እንዲሰጥም አድርጎታል። በሀገራዊ ግዳጅ ወቅት በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ጉዳት ገጥሞት በጉዳት ርቆ የነበረው ወጣቱ አማካይ ሙሉ በሙሉ ከጉዳት ማገገሙን ተከትሎ የሀዋሳን መለያ ዳግም የሚለብስም ይሆናል።