ሀዋሳ ከተማ የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውል አድሰዋል

ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን የግላቸው ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች የሁለት ነባሮችን ውል ደግሞ አራዝመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከጅምሩ ጀምሮ እየተካፈለ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በዛሬው ዕለት ወደ ዝውውሩ ጎራ በማለት ቢኒያም በላይ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ እና ወንድማገኝ ኃይሉን ያስፈረሙ ሲሆን አመሻሹን ደግሞ የሁለት ነባሮችን ውል አራዝመዋል።


ከወራቶች በፊት ሀዋሳን ተቀላቅሎ የነበረው አጥቂው እስራኤል እሸቱ ውሉ ተራዝሞለታል። በሀዋሳ ከተማ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች ውስጥ በመጫወት እግር ኳስን የጀመረው እና በዋናው ክለብም ዘለግ ያሉ ዓመታትን በማሳለፍ በመቀጠል በሰበታ ከተማ ፣ ወልቂጤ ከተማ እና መቻል ቆይታን ያደረገው የፊት መስመር አጥቂው እስራኤል እሸቱ ከአራት ወራት በፊት በግማሽ ወራት ወደ አሳዳጊ ክለቡ ተመልሶ የነበረ ሲሆን ውሉ መቋጨቱን ተከትሎ ተጨማሪ ዓመትን በክለቡ ለመቆየት ውሉ ተራዝሟል።

ወጣቱ የግብ ዘብ ምንተስኖት ጊምቦም ውሉን አራዝሟል። በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ ከወራት በፊት ወደ ሜዳ የተመለሰው እና በሊጉ በተጠናቀቀው ዓመት የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንታት ላይ ጥሩ ጊዜን ያሳለፈው ግብ ጠባቂው በሀዋሳ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች ውስጥ ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ ያለፉትን ዓመታት በዋና ቡድን ውስጥ እና ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድንም ተሰልፎ ተጫውቷል።