ሀዲያ ሆሳዕና የሦስት ተጫዋቾችን ኮንትራት አድሰዋል

የአሰልጣኝ ግርማ ታደሠን ውል ከቀናት በፊት ያራዘሙት ነብሮቹ የሦስት ነባር ተጫዋቾቻቸውን ውል በዛሬው ዕለት አራዝመዋል።

ወደ አዲስ የተጫዋቾች ዝውውር ከመግባታቸው በፊት የነባር ተጫዋቾችን ውል ማራዘም ቀዳሚ ተግባራቸው ያደረጉት እና ከቀናት በፊት የአሰልጣኝ ግርማ ታደሠን ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት ያራዘሙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በዛሬው ዕለት የሦስት ነባሮችን ኮንትራት አድሰዋል።


አይቮሪያኑ የተከላካይ እና የአማካይ ተከላካይ ቦታ ተጫዋቹ ከድር ኩሊባሊ ውሉን አራዝሟል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ከሀገር ውጪ መጥቶ በደደቢት በመቀጠል በፋሲል ከነማ እና ያለፈውን ዓመት ደግሞ በሀዲያ ሆሳዕና በመጫወት ከአስር ዓመታት በላይ በሀገራችን ሊግ ላይ የቆየው ተጫዋቹ ለአንድ ተጨማሪ ዓመት በነብሮቹ ቤት ይቆያል።

ሳሙኤል ዮሐንስም ውሉ ተዝራሟል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስን የጀመረው እና በመቀጠል በአማራ ውሃ ሥራ ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ መድን የአማካይ እና የግራ መስመር ተከላካይ ተጫዋቹ በድሬዳዋ ያሰለጠኑትን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ጥሪ ተከትሎ በተጠናቀቀው ዓመት ያሳለፈበት ሀዲያ ሆሳዕና ለተጨማሪ አንድ ዓመት የሚያቆየውን ውል አራዝሟል።

ወጣቱ ተከላካይ ቃለአብ ውብሸትም ለሁለት ተጨማሪ ዓመት በክለቡ ይቆያል። ከቡድኑ ወጣት ቡድን በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የአሰልጣኝነት ዘመን ያደገው ተጫዋቹ በሊጉ ከታዩ ድንቅ ወጣቶች መካከል አንዱነው።