ቁመታሙ የነብሮቹ የግብ ዘብ ወደ ደቡብ አፍሪካ አምርቷል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሀዲያ ሆሳዕና ያሳለፈው ግብ ጠባቂ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራቱ እርግጥ ሆኗል።

አንድ ሜትር ከዘጠና ሁለት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው አይቮሪያኑ የግብ ዘብ ቴፒ አልዛየር ከሁለት ዓመታት በፊት ባህር ዳር ከተማን በመቀላቀል የኢትዮጵያን እግርኳስ የተዋወቀ ሲሆን አንድ ዓመት በጣና ሞገዶቹ ቤት ግልጋሎት ሰጥቶ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አምርቶ ነበር። ተጫዋቹ በነብሮቹም ቤት ለአንድ ዓመት ከተጫወተ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊግ የሚያደርገውን ዝውውር እንዳገባደደ ታውቋል።

ከታዋቂው አስፓየር አካዳሚ የተገኘው እና ሀገሩን በተለያዩ የእድሜ እርከን ቡድኖች ያገለገለው ቴፒ በተጠናቀቀው የደቡብ አፍሪካ ሊግ (ቤት ዌ ፕሪምየር ሶከር ሊግ) 6ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀውን ቲ ኤስ ጋላክሲ በሁለት ዓመት ውል የተቀላቀለ ሲሆን ከቀናት በፊት ወደ ካይዘር ቺፍስ ለተዘዋወረው የቀድሞ የክለቡ ግብ ጠባቂ ፊያስሪ ታዋሪ ምትክ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።